የቤት ውስጥ ስራን ጥንቅቅ አድሮ የሚሰራው “ሮቦት የቤት ሰራተኛ”
ተመራማሪዎች ምግብ ማብሰል፣ ማፅዳትና ልብስ ማጠብን ከሰዎች መማር የሚችል ሮቦት ይፋ አድርገዋል
ሮቦቱ ከሰዎች ጋር መነጋር፣ የቤት እንስሳትን ማጫወትና አትክልት ውሃ ማጠጣትም ይችላል ተብሏል
በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ምግብ ማብሰል፣ ማፅዳትና ማጠብን ከሰዎች መማር የሚችል ሮቦት ይፋ አድርገዋል።
“ሞበይል አሎሃ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሮቦቱ ስራውን ራሱን ችሎ ማከናወን ወይም በተጠቃሚ ትእዛዝ ሊሰራ እንደሚችል ተነግሯል።
በጎማ የሚንቀሳቀሰው ሮቦቱ በአንድ ሰከንድ 1.6 ሜትር ይጓዛል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በአማካይ ከሰው ልጅ ፍጥነት ጋር የሚስተካከል መሆኑን ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል።
ተመራማሪዎች በለቀቁት የሙከራ ቪዲዮ ላይ ሮቦቱ ምግብ ሲያበስል፣ ሊፍት (አሳንሰር) ጠርቶ ሲሳፈር፣ በጠረጴዛ ላይ የተደፋ ቆሻሻ ሲያጸዳ፣ መጥበሻ ሲያጥብ ወንበሮችን እየገፋ ሲያስተካከል እና ከሰዎች ጋር ሲነጋገር አሳይተዋል።
በተጨማሪም በርቀት መቆጣጠሪያ (ሪሞት) አማካኝነት ልብስ በላውደሪ ማጠቢያ መጨመርና እንደሚያጥብ፣ የቡና ማፍያ ማሽን እንደሚጠቀም፣ በቫክዩም ክሊነር ቤት እንደሚያጸዳ፣ የእቃ ማጠቢያ ማሽን ውስጥ እቃ ማስገባት እና ማውጣት እንደሚችል፣ ከማቀዝቀዣ ውስጥ የሚጠጣ እንደሚያቀርብ፣ ቢራ መክፈት፣ ቆሻሻ መጣል፣ አትክልቶችን ማጠጣትና የቤት እንስሳትን ማጫወትን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን ይፈጽማል ብለዋል።
ስለአዲሱ ሮቦት መረጃ መውጣቱን ተከትሎ በርካቶች አስተያየት በመስጠት ላይ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን፤ አንድ የቀድሞ ትዊተር የአሁኑ X ተጠቃሚ በሰጠው አስተያየትም “በመጨረሻም ሊኖረን የሚገባ አዲስ ፈጠራ መጥቷል፤ ትልቅ የፈጠራ ስራ ነው” ሲል አድንቋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪም “ይሄን የት መግዘት እችላለሁ፤ በኩሽናዬ ውስጥ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ” ሲል አስተያየት ሰጥቷል
ይሁን እንጂ “ሮቦቱ ፍጹም አይደለም፤ ስህተቶችን ይሰራል” የሚሉት ተመራማሪዎቹ ሃርድዌሩም ሆነ ሶፍትዌሩ አሁንም “ውስንነቶች” ስላሉት መስተካከል አለባቸው ብለዋል።
ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አንዱ የሆነው ቶኒ ዣሆ፤ “አሁን ላይ ሮቦቶቹ ለገበያ ለመቅረብ ዝግጁ አይደሉም” ሲል አስተያየት ሰጥቷል።