የክርስቲያኖ ሮናልዶ አል ናስርን የሊጉ ዋንጫ ባለቤት የማድረግ ጉዞ
የሳኡዲ ክለቦች ባለፉት አመታት በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በአጠቃላይ 957 ሚሊየን ዶላር ወጪ አድርገዋል
የሳኡዲ ክለቦች ባለፉት አመታት በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በአጠቃላይ 957 ሚሊየን ዶላር ወጪ አድርገዋል
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአል ናስር ቆይታው ዋነኛ አላማ የሆነውን የአል ሂላል የበላይነት ለማስቆም ይህ አመት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሳኡዲ ሊግ ነገ የሚጀመር መሆኑን ተከትሎ ሮናልዶ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ “አዲስ የውድድር አመት ተመሳሳይ አላማ” ሲል የሊጉን ዋንጫ ለማሸነፍ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል፡፡
ለአመታት የሪያዱ አል ሂላል በበላይነት የነገሰበትን የሳኡዲ ሊግ በ2022 የተቀላቀለው ክርስቲያኖ እስካሁን የሊጉን ዋንጫ ማንሳት አልቻለም፡፡
ሳኡዲ በእግርኳሱ ውስጥ ስሟን እንደ ስፔን እና እንግሊዝ ለማስጠራት ትልቅ ፕሮጀክት ቀርጻ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች፡፡
ባለፉት ሶስት አመታትም በስመጥር የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችንም በከፍተኛ ክፍያ ሊጉን እየተቀላቀሉ ሲሆን ሮናልዶን ተከትለው ሊጉን የተቀላቀሉ ተጨዋቾችን ለማምጣት በአጠቃላይ 957 ሚሊየን ዶላር ወጪ ሆኗል፡፡
እንደ አጠቀላይ የሀገሪቱን ሊግ ተፎካካሪ እና ተወዳጅ ለማድረግ ያለው እቅድ እንዳለ ሆኖ እንደ አል ናስር ያሉ ቡድኖች ደግሞ የአል ሂላልን የበላይነት መቀልበስ እና የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ወጥነው በትኩረት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አል ሂላል በተጠናቀቀው የውድድር አመት 31 ጨዋታዎችን አሸንፎ ሶስት ጨዋታዎችን አቻ በመውጣት ሊጉን ማሸነፍ ሲችል የሮናልዶ አልናስር በ14 ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሳኡዲ ሱፐር ካፕ ሁለቱ ቡድኖች በነበራቸው ግጥሚያም አል ሂላል አል ናስርን 4ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡
በቡድኖቹ መካከል ያለው ተፎካካሪነት የአውሮፓ ተጫዋቾች በብዛት መምጣት ከመጀመራቸው በፊትም የነበረ ነው፡፡
ከቸልሲ የተዘዋወረው የአል ሂላል ተከላካይ ካሊዶ ኩሊባሊ “ሁሉም የሊጉ ተሳታፊዎች እኛ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረጋቸው አዲሱ የውድድር ዘመን ከባድ ሊሆን ይችላል” ሲል ተናግሯል፡፡
ነገር ግን የብራዚላዊው አጥቂ ኔይማር ከጉዳት መመለስ የቡድኑን ተፎካካሪነት ሊጨምረው እንደሚችል ነው የተነገረው
አል ሂላልን ከተቀላቀለ በኋላ አምስት ጨዋታዎችን ብቻ አድርጎ ግራ እግሩ ላይ ባጋጠመው ከባድ ጉዳት ከሜዳ ርቆ የነበረው ኔማር ልምምድ መስራት የጀመረ ሲሆን በመሰከረም ወር በሙሉ አቋም ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኔይማር ቦታ ሲጫወት የነበረው ሰርቢያዊው አጥቂ አሌክሳንደር ሚትሮቪች በሊጉ 28 ግቦችን ሲያስቆጥር ክርስቲያኖ ሮናልዶ 35 ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚው ነው፡፡
ሮናልዶ የአል ናስርን ህልም ለማሳከት ከሚገኝበት የእድሜ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የመጨረሻ እድሉ ይሄኛው የውድድር አመት እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
የሳኡዲ ክለቦች እንዳለፈው አመት በዝውውር መስኮቱ በስፋት እየተሳተፉ አይደለም ይሁንና አልናስር ብራዚላዊውን ግብ ጠባቂ ቤንቶን አስፈርሟል፡፡
የሮናልዶ ክለብ ከአልሂላል ባለፈ ሪያድ ማህሬዝ እና ካሪም ቤንዜማ ከሚገኙበት አል ኢትሀድ የሚገጥመው ፈተናም ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡