ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለምባፔ የደስታ ምልእክት ካስተላለፉት ውስጥ ቀዳሚው ነው
ፈረንሳዊው የፊት መስመር ተጨዋች ኪሊያን ምባፔ ሪያል ማደሪድን መቀላቀሉን ተከትሎ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን መቻ ተነግሯል።
ኪሊያን ምባፔ ለሪያል ማድሪድ እስከ 2029 የውድድር ዘመን የሚያቆየውን የአምስት አመት ኮንትራት መፈረሙም ይፋ የተደረገው ባለንበት ሳምንት ነው።
ኪሊያን ምባፔ የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድን በይፋ መቀላቀሉን ተከትሎም በማበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ በልጀነቱ የክለቡ ማሊያን ለብሶ እንዲሁም ከተጫዋቾቹ ጋር የተነሳቸውን ፎቶዎች በማጋራት ደስታውን ገልጿል።
ምባፔ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው ጽሁፍም "ህልሜ እውን ሆነ፤ሁሌም ወደማልመው ክለቤ ሪያል ማድሪድ በመቀላቀሌ ደስታ እና ኩራት ይሰማኛል” ብሏል።
ይህንን ተከትሎም ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለምባፔ በአስተያየት መስጫ ላይ ባስተላፈለት የደስታ መልእክት አዲስ ዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን መቻሉ ነው የተገለጸው።
ሮናልዶ ለምባፔ በአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ ባስተላለፈው ምልእክት አሁን “የእኔ ተራ ነው፤ በበርናባው ላይ ስታበራ ለማየት ጓጉቻለሁ” የሚል ነበረ።
ፖርቹጋላዊው የአል ናስር የፊት መስመር ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለምባፔ በኢንስታግራም ላይ የሰጠው አስተያየትም ከ4 ሚሊየን በላይ ላይክ (መውደዶችን) ማግኘቱ ተነግሯል።
በዚህም ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለኪሊያን ምባፔ የሰጠው አስተያየት በኢንስታግራም ላይ ከፍተኛ ላይክ ያገኘ አስተያየት በመሆን አዲስ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት መሆን ችሏል።
የ39 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳሱ ዓለም አሁንም አዳዲስ ክብረወሰኖችን ማስመዝገቡን እና መስበሩን ቀጥሎበታል።
ሮናልዶ 35 ግቦችን በማስቆጠር በሳውዲ ሊግ በአንድ የውድድር አመት ብዙ ጎል በማስቆጠር አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።
በተጨማሪም ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ4 የተለያዩ ሊጎች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ የመጀመሪያው ታሪካዊ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።
በእግር ኳሱ ዓለም የተለያዩ ክብረወሰኖች ባለቤት የሆነው ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከዚህ ቀደም “እኔ ክብረወሰኖችን አላሳድድም ክብረወሰኖች ራሳቸው ያሳድዱኛል እንጂ” ማለቱ አይዘነጋም።