ጉዞው በጀርመን ፣ በፖላንድ፣ በቡልጋሪያ እና በመሳሰሉት የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት የሚደረግ የትርዒት ጉዞ ነው
ከ25 ዓመታት በፊት በ1989 ዓ/ም ነው፤ ለጥበብ ፍቅር ባደረባቸው ወጣቶች የተቋቋመው፡፡ እንደ ቡድን ተሰባስቦ የራሱ አደረጃጀት ኖሮት መንቀሳቀስ ከጀመረበት ከዚያን ጊዜ አንስቶም በርካቶችን አፍርቷል፡፡ ስመ ገናናው ሰርከስ ደብረ ብርሃን፡፡
የሰርከስ ፍቅር ባደረባቸውና ተሰጥዖዋቸውን ለማሳደግ አጥብቀው ይሹ በነበሩ ወጣቶች የተመሰረተው ሰርከስ ደብረ ብርሃን ዛሬ ከሃገር አልፎ በአፍሪካ ብሎም በተለያዩ የዓለማችን ሃገራት ለመታወቅ ችሏል፡፡
ይህ በተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር በሆኑ አካታች የጥበብ ስራዎች የሚታወቅ የባለ ራዕይ ወጣቶች ስብስብ ልክ በተመሰረተ በ2 ዓመቱ ውስጥ የጀመረውን የውጭ ጉዞ ዛሬም ቀጥሎበት በተለያዩ የአውሮፓ እና የስካንዲኔቪያን ሃገራት የ3 ወራትን ቆይታ ለማድረግ ወደ ጀርመን አቅንቷል፡፡
ጉዞው በምን ምክንያት የሚደረግ ነው፣ ምንስ ይገኝበታል ስለሚለው እና ስለ ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች አል ዐይን አማርኛ ከሰርከሱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተክሉ (ሄኖክ) አሻግር ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡ አቶ ተክሉ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ብሔራዊ ሰርከስ ፕሬዝዳንትም ናቸው፡፡ ይዝለቁበት፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡ ሰርከስ ደብረብርሃን ወደ ውጭ ሃገራት ጉዞ እንዳለው ሰምተናል፡፡ ጉዞው በምን ምክንያት የሚደረግ ነው? ወዴትስ ነው የሚደረገው?
አቶ ተክሉ፡ እኔም አመሰግናለሁ፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ያለፉትን ሁለት ዓመታት ለመንቀሳቀስ ተቸግረን ነበር፤ አሁን ግን ተጽዕኖው በአንጻራዊነት መቅለሉን ተከትሎ በአውሮፓ ለሶስት ወራት የሚዘልቅ ጉዞ ልናደርግ ነው፡፡ ጉዞው ስራዎቻችንን ለማቅረብ የሚያስችል የትርዒት ጉዞ ነው፡፡ በይዘቱ ከወትሮው ተለይቶ ስልጠና (ወርክ ሾፕ) ተኮር ሆኖ ስራዎች የሚቀርቡበ ነው፡፡
በጀርመን ረዘም ላለ ጊዜ፣ በፖላንድ፣ በቡልጋሪያ እና በመሳሰሉት የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ቆይታ እናደርጋለን፡፡ ቆይታችን በየደረጃው ካለው እስከታችኛው ማህበረሰብ ድረስ የሚያገናኘን ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ከአሁን ቀደም ባደረጋችኋቸው ጉዞዎች የተለያዩ ስራዎችን ይዛችሁ ትሄዱ ነበር፡፡ ለዚህም “ካርጎ” የተሰኘውንና በስደት ጉዳዮች ላይ ያተኮረውን ስራችሁን ማንሳት ይቻላል፡፡ አሁን ምን ይዛችሁ ነው የምትሄዱት?
አቶ ተክሉ፡ ልክ ነው፡፡ በ2013/14 (እ.ኤ.አ) ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስብል ሁኔታ ስዊድን ለሚገኝ አንድ ትያትር ቤት አንድ “ካርጎ” የተሰኘ ሙሉ ‘ፕሮዳክሽን’ ሰርተን አቅርበናል፡፡ የተለያዩ ሽልማቶችንም አግኝተንበታል፡፡
አሁንም በኢትዮጵያ ያሉ ወጣት ሴቶች በየደረጃው የሚገጥሟቸውን ፈተናዎችን እና ተጽዕኗቸውን የሚያሳይ ትርዒት ነው ያዘጋጀነው፡፡ “ህልም አለኝ” ይሰኛል፡፡ የኢትዮጵያን እሴቶች በሚያሳይ መልኩ ዓለም አቀፍ ይዘቶችን እንዲላበስ አድርገን አዘጋጅተነዋል፡፡ እሱን ይዘን ነው የትርዒት ጉዞውን የምናደርገው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ከሌሎች ቡድኖች ምን የተለየ ሰርታችሁ ነው አሁን ወደ ውጭ የምትወጡት?
አቶ ተክሉ፡ የተሻለ ተሰጥዖ እና ክህሎት ያላቸው ብዙ ቡድኖች እዚህ ሃገር ውስጥ አሉ፡፡ እኛ ግን ሰርከሱን ሰፋ አድርገነው የህብረተሰቡን ችግሮች ወደሚያነሳ አዝናኝ አካላዊ ትርዒት ከፍ አድርገነዋል፡፡ በዚህ መልኩ አዋህዶ ማቅረቡ ነው የእኛ ትልቁ ልምድ፡፡ ማንንም ብትጠይቅ ይሄን ይነግሩሃል፡፡ በተለያዩ የዓለም ሃገራትም ይህንኑ ልምዳችንን እናካፍላለን፤ ስራዎቻችንንም እናቀርባለን፡፡ እኔም በትምህርት ያገኘህትን እውቀት ካለኝ ልምድ ጋር በማጣጣም ነው ሰርከሱን የምመራው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ሰርከስ ደብረብርሃን ከአሁን ቀደም በነበሩት ጉዞዎች አካል ጉዳተኞችን ጭምር አካቶ ይጓዝ ነበር፡፡ አሁን እነማንን ይዞ ነው የሚጓዘው?
አቶ ተክሉ፡ ልክ ነው፤ ሰርከስ ደብረብርሃን አካታችነቱ ነው ለየት የሚያደርገው፡፡ የተለያየ አካል ጉዳት ያለባቸው ልጆች ራሳቸውን በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች በሙዚቃ፣ በዳንስ እንዲሰለጥኑ እናደርጋለን፡፡ ‘ፕሮፌሽናል’እንዲሆኑም ሰርተናል፤ አሁንም እየሰራን ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች ሆነው ‘ፕሮፌሽናል’ ሰርከስ ሰራተኞችንም አፍርተናል፡፡ ከነዚህ መካከል መስማት የተሳናት ሃብታምነሽ አንዷ ናት፡፡ ስለዚህ ሃብታምነሽ የዚህ ጉዞ አካል ናት ማለት ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ለሶስት ወራት ከሚዘልቀው የውጭ ጉዞ ምን ሊገኝ ይችላል?
አቶ ተክሉ፡ የሃገራችንን ገጽታ በተለያዩ ስራዎች እናስተዋውቅበታለን፡፡ እኛ ከዓለም የምንወስደው ብቻም ሳይሆን የምናሳየው ፣ ስለ ዓለም ሰላምና ሴቶች የምንለው ነገር እንዳለን እናሳይበታለን፡፡ እኛም ጋር የተለያዩ ተሰጥዖዎች እንዳሉንም የምናሳይበት ነው፡፡ በዋናነት ታሪክን ባህልን የማሳየት ስለ ሰላም የመናገር ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ሰርከስ ደብረብርሃን ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ጥቂት የማይባሉ ልጆች የያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃም ለተለያዩ ሪከርዶች የሚታጭ ነበረ፡፡ አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?
አቶ ተክሉ፡ ጥሩ ነው ያለነው ወረርሽኙ ያመጣብንነ ነገር ቢኖርና ቢያስተጓጉለንም፡፡ እኔ በሀገርም ደረጃ የብሄራዊ ሰርከስ ፕሬዝዳንት የሁሉንም ደረጃ አያለሁ እና ሰርከስ ደብረ ብርሃን ከአፍሪካ ይደለም በዓለምም ጭምር ተጠቃሽ ሊያደርገው በሚችል ጥሩ የ‘ታለንት’ ደረጃ ላይ እንደደረሰ እና እንደሚገኝ ለመናገር እችላለሁ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ሰርከስ ደብረ ብርሃን መቼና እንዴት ነው የተመሰረተው?
አቶ ተክሉ፡ በ1989 ዓ/ም ነው፤ ያላቸውን ፍላጎትና ተሰጥዖ ለማሳደግ በሚፈልጉ የደብረብርሃን ወጣቶች የተቋቋመው፡፡ በወቅቱ በነበረው ስፖርት ኮሚሽን ደጋፊነት ቡድን ሆነው ከኢትዮጵያ ሰርከስ አሰልጣኝ ተልኮላቸው በአሰልጣኝ ነጻነት አሰፋ አስተባባሪነት ህጋዊ ሆኖ የተመሰረተ ነው፡፡ ነጻነት ደግሞ እኔን በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ አብሬው እንድሰራ አድርጎኛል፡፡
ሰርከስ ደብረብርሃን ብዙ ጊዜ ለየት ያሉ የፈጠራ እና የሃሳብ ስራዎችን አካል ጉዳተኞችን ጭምር አካቶ ነው የሚሰራው፡፡ በወቅቱ ‘አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የመጀመሪያ ሰርከስ በአፍሪካ’ እየተባለ ዜናዎች ይሰሩልንም ነበረ፡፡ በተመሰረተ በ2 ዓመት ውስጥ ነው የውጭ ጉዞ ያደረገው፡፡ ከዚያም ወዲህ በየዓመቱ እያደረገ ነው፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ ከ25 ዓመታት በፊት የሆነ ነው፡፡ ሰርከሱንም ለተለያዩ ለማህበረሰብ ልማቶች እንደ ማንቂያ በሂደት እያሳደግን ተጠቅመንበታል፡፡ ከዚያ ውጭ የሙያ እና የዓላማ ነጻነት ኖሮን በራሳችን ስንሰራ ነው የቆየነው፤ ይህ ጠቅሞናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የራሳችን የልምምድ እና የስራ ቦታ ቢሮዎች አሉን፡፡ ማንም ሳያግዘን በራሳችን አቅም ይህን ለማድረግ መቻላችን ቀላል አይደለም፡፡ ሌላኛው የሰርከሱ አባል የሆኑ አርቲስቶች ዓላማ ቁርጠኝነት ያላቸው ተባብሮ መስራት የሚችሉ መሆናቸው ረድቶናል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ ሰርከስ ደብረ ብርሃን አሁን ያለው የአባላትና የስራ አደረጃጀት ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ተክሉ፡ ሲጀመር ጀምሮ በተለያዩ የስራ ክፍሎች ተደራጅቶ ነው የሚሰራው፡፡ በዋናው አደረጃጀታችን ደግሞ 42 አካባቢ ልጆችን ይዘን ነው የምንሰራው፡፡ የባህል ሙዚቃ ቡድን (ባንድ) አለን፡፡ ቡድኑ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችንና ሙዚቀኞችን የያዘ ነው፡፡ ሰርከሱን የሚሰሩ ፕሮፌሽናል አርቲስቶችን የያዘ ቡድንም አለን፡፡ እነዚህ 42 አካባቢ ናቸው፡፡ በአባላት ብዛት እያደገ እየሰፋ ነው የመጣው፡፡ አሁን ለምሳሌ ክረምት ላይ ያሉን የመስሪያ ቁሳቁሶች እስከሚያጥሩን ድረስ ከመቶ በላይ ልጆች ወደእኛ መጥተው አብረን ስንሰራ ነበር፡፡ ትምህር ቤትም ነገር አለን እስከ 70 ድረስ ልጆችን እንይዛለን፡፡ እንዲያውም አሁን ያለው የተጠቃሚነት ቤተሰብን የመደጎሙ ሁኔታ እያደገ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም አባላትን ለማግኘት ትምህርት ቤቶች ላይ ቀስቅሰን አስተዋውቀን ነበር፡፡ አሁን ግን ራሱ ቤተሰብ ነው ልጄ የሰርከስ አርቲስት መሆን ይፈልጋል ብሎ ይዞ የሚመጣው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ በቀጣይ በተለይም ከውጭ ስትመለሱ ልትሰሩ የምታስቧቸው ነገሮች ምንድናቸው
አቶ ተክሉ፡ አሁን የወረርሽኙ ሁኔታ በአንጻራዊነት ቀለል ያለ ይመስላል፡፡ እኛም መንግስት ባስቀመጣቸው መመሪያዎች መሰረት እንሰራለን፡፡ ስንመለስ ደግሞ የወሰድናቸውን ልምድና ተሞክሮዎች እውቀቶች ማምጣት ነው፡፡ ያለንን የቁሳቁስ የክህሎት አቅም እንገነባለንም ብለን አስበናል፡፡ ደብረ ብርሃን ላይ ደረጃውን የጠበቀ ባህል ማዕከል ለመስራት የጀመርነው ስራ አለ፡፡ እሱን ማጠናቀቅ ለይደር የማንተወው ስራ ነው፡፡ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንቀጥላለንም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ተክሉ፡ እኛም እናመሰግናለን፡፡