ማይክል ለዓለም ጀባ ባለቸው ድንቅ አልበሞቹ እ.ኤ.አ 1984 የፖፕ-ንጉስ “ኪንግ ኦቭ ፖፕ” የሚል እውቅና አግኝቷል
በ20ኛው ክ/ዘመን በዓለማችን ዝናንና ክብርን ከተጎናጸፉ እውቅ የዓለማችን አርቲስቶች አንዱ ነው፤ አሜሪካዊው አቀንቃኝ፣ የዜማ ደራሲ እና ዳንሰኛው የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጆሴፍ ጃክሰን (ማይክል ጃክሰን)፡፡
አምስት አባላት ካሉት የጃክሰን ቤተሰብ እና ከአሜሪካዋ የኢንድያና ግዛት የተገኘው ማይክል ፤ወደ ኪነ-ጥበቡ ዓለም ተቀላቅሎ የዓለም ጥበብ አፍቃሪያንን ቀልብ መሳብ የጀመረው ገና እ.ኤ.አ 1980ቹ አጋማሽ ላይ ነበር፡፡
ማይክል ጃክሰን እ.ኤ.አ 1979 -ኦፍ ዚ ዎል- /Off the Wall/ በተሰኘ ርዕስ የለቀቀው የመጀመርያ አልበም ከተጠበቀው በላይ የዓለም ቀልብን የሳበና 20 ሚልዮን ኮፒዎች የተሸጡበት ነበር፡፡
የአልበሙ “ዶንት ሰታፕ ቲል ጌት ኢናፍ” እና “ሮክ ዊስ ዩ” የተሰኙ ስራዎችም የማይክል ጃክሰን ድንቅ አቅምና ዘመናዊ የዲስኮ ዳንስ ጥበብ የታዩበት ነበር፡፡
ከሶስት አመታት በኋላ ያስከተለው ሌላው “ትሪለር” የተሰኘ አልበም ደግሞ ማይክል ዝናውን በዓለም እንዲናኝ ምክንያት የሆነበት በሰው ልጆች ልብ ህያው እንዲሆን ካስቻሉት ስራዎቹ የሚጠቀስ ነው፡፡
ማይክል የተለያዩ የሶሎ ድንቅ አልበሞች ይዞ ለዓለም ህዝብ ጀባ በማለቱም እ.ኤ.አ 1984 የፖፕ-ንጉስ “ኪንግ ኦቭ ፖፕ” የሚል እውቅና ማግኘት ችሏል፡፡
በሙዚቃ ስራዎቹ ዓለም ቆሞ ያጨበጨበለት ማይክል ጃክሰን፤ በተለይም ከ1990ዎቹ አንስቶ የህይወት ዘይቤውም እጅግ አከራካሪ ሆኖ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም አላበቃም 1993 ላይ ጓደኛው በሆነው የ13 ዓመት ልጅ ጾታዊ ጥቃት ፈጽሟል በሚል መከሰሱ፣ እ.ኤ.አ 1994 ከ“ሮክ ንጉሱ” ኢልቭስ ፕርስሌይ ሴት ልጅ ሜሪ ፕርስሌይ ያደረገው ሁለት አመታት እንኳን እንዳልዘለቀ የሚነገርለት ሚስጥራዊ ጋብቻ እንዲሁም የነበረውን ኃብት ሁሉ እስከመሸጥ ያደረሰው የፋይናንስ ቀውስ የዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡
እነዚህ የማይክል ገመናዎች በተለይም በአሜሪካ የማይክል ምስል እንዲጠለሽ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
ማይክል የነበረውን ምስል ለመመለስ እና ከአድናቂዎቹ ጋር ዳግም ለመገናኘት በመጨረሻዎቹ ሰአታት ኮንሰርት ለማቅረብ በልምምድ ላይ የነበረ ቢሆንም፤ የልብ ህመም ቀድሞት ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 25፤2009 የተሰማው የማይክል ሞት ዓለምን ሁሉ ያስደነገጠ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
ማይክል ጃከስን ገና ብዙ መስራት በሚችልበት 50 ዓመቱ ህይወቱ ቢልፍም ፤በማይረሱት ስራዎቹ በሰው ልጆች ልብ ህያው ሆኖ ዛሬም ድረስ የዘለቀ ድንቅ የዓለማችን አርቲስት ሆኗል፡፡