በስህተት ለፈረሰ ቤቱ የማፍረሻ ወጪውን እንዲከፍል የተጠየቀው አሜሪካዊ
በአትላንታ ከተማ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ የማፍረሻ ወጪውን 68 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተጠይቋል
ግለሰቡ ቤቱ በስህተት ፈርሶበት ካሳ ሲጠብቅ ክስ ደርሶታል
በአሜሪካ አትላንታ ከተማ ቤቱ በስህተት የፈረሰበት ግለሰብ ሌላ ችግር ገጥሞታል።
ኤቨርት ትሪፖዲስ የተባለው ግለሰብ ከጥቂት ወራት በፊት ከእናቱ ጋር በምዕራባዊ የከተማዋ ክፍል ከ100 አመት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ ቤት ይገዛሉ።
ይህን ታሪካዊ መኖሪያ ቤት ምቹ ለማድረግ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ግን በአንድ ማለዳ ፈራርሶ ይጠብቀዋል።
የቻናል 2 የቴሌቪዥን ጣቢያም ጉዳዩን በምርመራ ዘገባው ሽፋን ይሰጠዋል።
በዚህ ዘገባ ትሪፖዲስ ቤቱ ለመኖሪያ ምቹ አይደለም የሚል ማስጠንቀቂያ እና እንዲያድስ የሚያሳስብ ደብዳቤ እንዳልደረሰው ሲናገር ይደመጣል።
የከተማዋ አስተዳደር ካልታደሰ ይፈርሳል የሚል ማስጠንቀቂያውን የላከው ለሌላ አካባቢና የቤት ቁጥር መሆኑን የሚያሳዩ ደብዳቤዎችንም የምርመራ ዘገባው ይፋ ያደርጋል።
ቤት የሚያፈርሰው ኩባንያ የተጻፈለት ደብዳቤም የትሪፖድስ ቤት ትክክለኛ አድራሻ አልነበረም።
ዘገባው ከተላለፈ በኋላ በአንድ ቀን ታሪካዊ ቤቱ የፈራረሰበት ትሪፖዲስ ከከተማው አስተዳደር ደብዳቤ ይደርሰዋል።
“ደብዳቤው ሲደርሰኝ ደስ ብሎኝ ነበር፤ በስህተት ቤቴን ስላፈረሱበት ምክንያት ሊያስረዱኝ እና ይቅርታ ሊጠይቁኝ ይሆናል፤ ምናልባትም የካሳ ክፍያ ቼክ ጽፈውልኝ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፤ ነገር ግን የክስ ደብዳቤ ሆኖ አገኘሁት” ይላል ትሪፖዲስ።
ቤቱ በስህተት የፈረሰበት ግለሰብ ቤቱን ለማፍረስ የወጣውን ወጪ ከነወለዱ 68 ሺህ ዶላር ይከፍል ዘንድ ተጠይቋል፤ ክስም ተመስርቶበታል።
ግለሰቡ አስቀድሞ የከተማውን አስተዳደር በስህተት ቤቴን አፍርሷል በሚል ቢከስም እስካሁን በፍርድ ቤት ጉዳዩ አልታየም ተብሏል።