ያለፍላጎቱ የልደት በዓሉን ያከበረለትን ድርጅት የከሰሰ አንድ ሰራተኛ 450 ሺህ ዶላር ካሳ ተከፈለው
ክስ የቀረበለት ፍርድ ቤትም ድርጅቱ ካለሰራተኛው ፈቃድ ማክበር አልነበረበትም ብሏል
ሰራተኛው የልደት በዓሉ ለድንጋጤ ዳርጎኛል ሲል ክስ መስርቷል
የልደት በዓሉን ያለፍላጎቱ ያከበረለትን ድርጅት የከሰሰ አንድ ሰራተኛ 450 ሺህ ዶላር ካሳ ተከፈለው፡፡
መሰረቱን በአሜሪካዋ ኬንታኪ ግዛት ያደረገው ግራቪቲ ዲያግኖስቲክስ የተሰኘው ድርጅት የሰራተኞቹን የልደት በዓል ያከብራል፡፡
ይህ የተቋሙ አንድ አሰራር ሲሆን አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ የድርጅቱ ሰራተኛ የልደት በዓሉ እንዳይከበርለት አስቀድሞ ይጠይቃል፡፡
ይሁንና ድርጅቱ የዚህን ሰራተኛ ልደት እንደ ሌሎች ሰራተኞች የልደት በዓሉን ለማክበር አስቦ ዝግጅቶችን ያደርጋል፡፡
ሰራተኛወም በአሰሪው ተበሳጭቶ የተዘጋጁለትን የልደት ኬኮች እና ሌሎችንም ስጦታዎች በመተው ከቢሮ ይወጣል፡፡ በሰራተኛው ድርጊት የተበሳጨው ቀጣሪው ድርጅቱም ሰራተኛውን ከስራ አሰናብቷል፡፡
ተቋሙ በድሎኛል ያለው ሰራተኛውም የልደት በዓሉ በስራ ቦታዬ ድንጋጤ ውስጥ እንድገባ እና ከዚህ በፊት የነበረብኝን የአዕምሮ ህመም አባብሶብኛል ሲል አሰሪውን ከሷል፡፡
የኬንታኬ ፍርድ ቤትም ግራቪቲ ዲያግኖስቲክ የተሰኘው ተቋም የልደት በዓሉን ሲያከብር የሰራተኛውን ፍላጎት እና የአዕምሮ ህመምን ግንዛቤ ውስጥ ሳይስገባ አከናውኗል በሚል የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የድርጅቱ ድርጊት ሰራተኛውን ለተባባሰ የአዕምሮ ህመም ዳርጎታል ያለው ፍርድ ቤቱ ድርጅቱ ሰራተኛው ለተፈጠረበት የስሜት ጉዳት 300 ሺህ ዶላር እንዲሁም 150 ሺህ ዶላር ደግሞ ስራ አጥ ለሆነባቸው ወራት በድምሩ 450 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ወስኗል፡፡