በ3 ነዋሪዎች ተቃውሞ ከመፍረስ የተረፈው አፓርትመንት መስህብ ሆኗል
በቻይና ጉዋንዞ የሚገኘው ባለስምንት ፎቅ ህንጻ ለመንገድ ስራ እንዲፈርስ ታስቦ ነበር
ሶስት የአፓርትመንቱ ባለቤቶች ለአልሚዎች ያቀረቡት ጥያቄ ባለመመለሱ ግን ህንጻው ሳይፈርስ የቀለበት መንገድ ተሰርቷል
በቻይና ጉዋንዙ ግዛት ሃይዙ በተባለው አካባቢ የሚገኘው ባለስምንት ፎቅ የመኖሪያ ህንጻ በፈረንጆቹ 2008 ለመንገድ ግንባታ በሚል ሊፈርስ ነበር።
በአፓርትመንቱ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎችም ከአልሚው ጋር ስምምነት ፈጽመዋል።
ይሁን እንጂ ሶስት ሰዎች ያስቀመጥነው ቅድመ ሁኔታ ካልተሟላ ቤታችን አይፈርስም በሚለው አቋማቸው ጸኑ።
ጉዋ ዢሚንግ እና ወንድሞቹ ለ30 ካሬሜትር ቤታቸው 400 ሺህ የቻይና ዩዋን ካሳ ቢሰጣቸውም አልተቀበሉም።
መንገዱን የሚገነባው አካል በተደጋጋሚ ለማግባባትና ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል ቃል ቢገባም ግለሰቦቹ “ቤታችን ለቀን አንወጣም” አሉ።
የሶስቱን ዜጎች አቋም ያከበረው አልሚ መፍትሄን አበጀ፤ ቤቱ ሳይፈርስ መንገድ የሚገነባበትን ዲዛይንም አቅርቦ ወደ ስራ ገባ።
እናም ሊፈርስ ቀናት ቀርተውት የነበረው ባለስምንት ፎቅ ቢጫ ህንጻ ሳይፈርስ ዙሪያውን ተሽከርካሪዎች የሚርመሰመሱበት የቀለበት መንገድ ተሰራ።
በሶስቱ ነዋሪዎች ከመፍረስ የተረፈውና በመንገድ የተከበበው ብቸኛ ህንጻ አሁን የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ሆኗል።
በተለያዩ ሀገራት መንግስትም ሆነ ሌሎች አልሚዎች ዜጎችን ለልማት በሚል ከቀደመ መኖሪያቸው ሲያስነሱ ተገቢውን ምትክ ቦታ እና ካሳ አይሰጡም የሚለው ቅሬታ ተደጋግሞ ይሰማል።
በጉዋንዙ እንደሆነው አይነት ለመነሳት ፈቃደኛ ላልሆኑ ዜጎች ሁሉንም የሚያስማማ መፍትሄን የሚፈልጉት ጥቂቶች ናቸው።