አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከ10 ቀናት በኋላ ወታደራዊ ልምምድ ያደርጋሉ
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገሪቱን ጦር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ከስልጣን ማንሳታቸው ተነገረ።
ኪም በስም ባይጠቅሷቸውም የፒዮንግያንግ ጠላት ናቸው ያሏቸው ሀገራትን ለመመከት ከፍተኛ ወታደራዊ ዝግጅት እንዲደረግም አሳስበዋል።
የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው የሀገሪቱ ጦር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ፓክ ሱ ኢል ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ከስልጣናቸው የተነሱበት ምክንያት ግን በዘገባው አልተጠቀሰም።
ጀነራል ፓክ የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት ጀነራል ሪ ዮንግ ጊል መተካታቸውም ተገልጿል።
ጀነራል ሪ ከዚህ ቀደምም የሰሜን ኮሪያ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው ማገልገላቸውን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ሪ በ2016 ከስልጣን ተነስተው ለወራት ከእይታ መራቃቸውን ተከትሎም የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙሃን ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ሲዘግቡ ነበር።
ኪም ጆንግ ኡን መደበኛ ያልሆነ ጦርን ሲመሩ የቆዩትን ጀነራል ሪ ዮንግ ጎልን የሾሙት ፒዮንግያንግ ከፍተኛ ወታደራዊ ዝግጅት እንድታደርግ በማሰብ ነው ተብሏል።
መሪው የሀገሪቱ የጦር መሳሪያ ምርት አቅም እንዲያድግ መመሪያ መስጠታቸውም ተገልጿል።
የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሽሩ ዋነኛ ምክንያት በይፋ ባይነገርም ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ስጋት እንደገባት እንደሚያሳይ ነው የተነገረው።
ኪም ባለፈው ሳምንት የሀገሪቱን የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ሲጎበኙ በአለም ካርታ ላይ ሴኡል እና አካባቢውን እየጠቆሙ ሲነጋገሩ ታይቷል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከ10 ቀናት በኋላ ከሚጀምሩት ወታደራዊ ልምምድ አስቀድሞም ፒዮንግያንግ አዳዲስና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቿን እንድትሞክር ኪም አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም የዋሽንግተን እና ሴኡልን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በሚሳኤል ማስወንጨፍ ስትቃወም የቆየችው ሰሜን ኮሪያ በ2022 ብቻ ከ100 በላይ ሚሳኤል መሞከሯ ይታወሳል።