የአባይ ውሃን በተመለከተ በካምፓላ የተካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያን ያላካተተና ተቀባይነት የሌለው ነው ተባለ
ስብሰባው ኢትዮጵያ ያልተጋበዘችበትና የማይታወቅ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ም/ቤት የገለፀው
ደካማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው ጫና ተቀባይነት እንደሌለውም የም/ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ትነበብ ብርሃኔ ተናግረዋል
የናይል ውሃን በተመለከተ በቅርቡ በካምፓላ የተካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያን ያላካተተ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ የሲሺል ማህበረሰብ ምክር ቤት ገለፀ፡፡
ራሳቸውን የአፍሪካ ውሃዎች ለሰላም፣ ናይል ለሰላም ሲቪል ማህበረሰብ ኢንሼቲቭ ብለው የሚጠሩትና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተቋማት በቅርቡ በካምፓላ መሰብሰባቸው የሚገልፅ ሰነድ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ስብሰባውን ተከትሎ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማቱ “በናይል ተፋሰስ አገራት የናይል ውሃ አጠቃቀምን እና በአፍሪካ የውሃ ብዝበዛ” በሚል ርእስ መግለጫ ማውጣታቸውንም አስታውቋል።
ይህ ስብሰባ በናይል ተፋሰስ ትልቁ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ያልተጋበዘችበትና የማይታወቅ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ምክር ቤት በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ያስታወቀው።
የምክር ቤቱ ም/ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ትነበብ ብርሀኔ “ስብሰባው ኢትዮጵያን ያላካተተ እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለውታል፡፡ ስበሰባው ኢትዮጵያ እየገነባቸው ካለው ግድብ ጋር ተያይዞ ሌላ ዓለማ ሊኖረው እንደሚችልም ጭምር ጠቁመዋል፡፡
ግድቡ ኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ውጪ ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል ነው ያሉ ሲሆን፤ ግብጽ የኮሎኒያል ዘመን ስምምነት እንዲተገበር የምታደርገውን ጥረት ሁሉም የተፋሰሱ አባል ሀገራት ሊቃወሙት እንደሚገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
“ሁሉም የግብርና ስራቸው ከዚህ ወንዝ ሆኖ ሳለ፣ ሱዳንም ይሁን ግብጽ እስካሁን ከኢትዮጵያ ላገኙት ውሃ እና አፈር ከፍለው አያውቁም” ሲሉም ነው ምክትል ፕሬዝዳንቷ የሀገራቱን ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ኮንነዋል።
ወ/ሮ ትነበብ ደካማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው ጫና ተቀባይነት የለውም፤ የህዳሴ ግድብ ዋነኛ ዓላማ ኤሌክትሪክን ማዳረስ ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ካለማንም ድጋፍ በራሷ አቅም መጀመሯን በማስታወስ፤ “ፕሮጄክቱ በማንኛውም አካል ላይ ጉዳት አያደርስም፣ ይህም በሱዳናውያን ምሁራን በተደጋጋሚ ተረጋግጧል፤ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በቅርቡ ይህንን አረጋግጠዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡
ግድቡ በማንም ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ከተረጋገጠ፣ ለምን ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትገነባ ተፈለገ የሚል ጥያቄም አቅርበዋል።
“ራሱን የአፍሪካ ውሃዎች ለሰላም፤ ናይል ለሰላም ሲቪል ማህበረሰብ ኢንሼቲቭ ብሎ የሚጠራው ስብስብ ያወጣው ሰነድ የመረጃ እጥረት እንዳለው ያመለክታል፤ እንዲህ አይነቱ በመረጃ ያልዳበረ መግለጫ ለአፍሪካ አይጠቅማትም” ብለዋል።
ሲቪል ማህበረሰብ አካላት ትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው መስራት ሲገባቸው፤ አሁን ያለውን አለመግባባት የሚያጋግል ተግባር ላይ መሳተፋቸውም ተገቢነት የሌለው መሆኑንም አስታውቀዋል።
ስለዚህም የኢትዮጵያ የሲሺል ማህበረሰብ ምክር ቤት ራሱን የአፍሪካ ውሀዎች ለሰላም፤ ናይል ለሰላም ሲቪል ማህበረሰብ ኢንሼቲቭ የሚጠራው ስብስብ ያወጣው ሰነድ ተቀባይነት እንደሌለው በማንሳት፤ ሰነዳቸውን በእውነት ላይ በተመሰረተ መልኩ ዳግም ሊያጤኑት እንደሚገባም ጠይቋል።