“የሕዳሴ ግድብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምስራቅ አፍሪካ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ያደርጋል” - ዶ/ር ስለሺ
በቀጣይ 240 የፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን በመገንባት 35 ሚሊዮን ሰዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል
27 ሺህ ሰዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ማዕከላት ዛሬ ተመርቀዋል
የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምስራቅ አፍሪከ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ አስታወቁ።
ዶ/ር ስለሺ በቀለ ይህን ያሉት ፣ በዛሬው እለት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ በ“ብርሀን ለሁሉም” ፕሮጄክት የተገነቡ ሦስት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ማእከላት መመረቃቸውን አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ ነው።
ሚኒስርሩ እንዳሉት በፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩት ሦስቱ ማዕከላት ፣ በምስራቅ ባሌ እና ምስራቅ ሀረርጌ የሚገኙ ከ27 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው።
ማዕከላቱ ባጠቃላይ በ160 ሚሊዮን ብር ወጪ በቅርብ ወራት ከተገነቡ 12 የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች መካከል መሆናቸውንም ነው ዶ/ር ስለሺ የጠቀሱት፡፡
በቅርቡም በ9 ክልሎች ውስጥ ግንባታቸው የሚካሄዱ 25 የፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማዕከላት ግንባታ እንደሚጀመርም ዶ/ር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል።
በሦስተኛ ምእራፍም 240 የፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማዕከላት ግንባታ እንደሚከናወን የገለጹ ሲሆን፤ ይህም በቀጣይ 5 ዓመታት በ“ብርሀን ለሁሉም” ፕሮጄክት 35 ሚሊየን ሰዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘ እቅድ አካል ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ አክለውም ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የኤልክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።
ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆተሩ ሰዎች የኤልክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።