በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃትና ግድያ እየተፈፀመብን ነው- ነዋሪዎች
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል
አስተያየት ሰጭዎቹ መንግስት ህይወታቸውን ብቻ እንዲታደግላቸው ጥሪ አቅርበዋል
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን የኪረሙ ወረዳ ነዋሪዎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው መሆኑን ገለጹ።
በወረዳው ሀሮ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ስማቸው በአካባቢው ባለው ግድያ ምክንያት እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጭ ለአል ዐይን አማርኛ በስልክ እንደተናገሩት በሀሮ ከተማ ከትናንት ቀን ጀምሮ ጥቃት ተከፍቷል።
በተከፈተው ጥቃት በወረዳው የሚኖሩ ዜጎች “አማራ በመሆናቸውን ብቻ” እየተገደሉ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተከፈተው ማንነትን መሰረት በማድረግ መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ መንግስት ህይወታቸውን ብቻ እንዲታደግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
“አሁን ላይ ህይወታችን አደጋ ላይ ነው፤ መቸ እንደምንሞት አናውቅም ከፍተኛ ጥቃት እየተፈጸመብን ነው“ ያሉት ደግሞ ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ ናቸው። በወረዳው አንዲት አካባቢ ብቻ ዛሬ አራት ሰዎች ተገድለው አስክሬናቸው ን አንስቶ መቅበር አለመቻሉን ነዋሪው ይናገራሉ።
ከዚህ ባለፈም ትናንት እንደተከፈተ በተገለጸው ጥቃት ስምንት ሰዎች መጎዳታቸውንም ነዋሪዎቹ ለአል ዐይን ገልጸዋል።
አል ዐይን አማርኛ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ባሉ ዜጎች ዙሪያ ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ያቀረበው ጥያቄ ምለሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር፤ የኪረሙ ወረዳ አስተዳዳሪ እንዲሁም የወረዳው ጸጥታ ጽ/ቤትን ምላሽ ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ከዚህ ባለፈም የኦሮሚያ ክልልን አቋምና ምላሽ ለማካተት ለክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ስልክ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ምላሹን መያዝ አልተቻለም።
መስከረም መጀመሪያ ሳምንታት አካባቢ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪረሙ ወረዳ የሚገኙ ሲቪል ሰዎች ደኅንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ መሆኑ እንደሚያሳስበው መግለጹ የታወሳል።
በዚሁ ወረዳ፣ ቦቃ ቀበሌ መስከረም 7 እና 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በደረሱ ሦስት ተያያዥ ጥቃቶች በአጠቃላይ 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፤ እንዲሁም መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም በውልማይ ቀበሌ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።
በኪረሙ ወረዳ ባለው አሳሳቢ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ከተለያዩ የወረዳው አካባቢዎች ተፈናቅለው በኖሌ ቀበሌ፣በሀሮ እና ኪራሙ ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለወራት አስቸኳይ ሰብአዊ ዕርዳታና ሌሎች ድጋፎችን ባለማግኘታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ከዚህ በፊት ገልጸው ነበር።
ኢሰመኮ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በኪራሙ ወረዳ ላለው የፀጥታ ስጋት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎችን ከሕግ ፊት ለማቅረብ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ማሳሰቡ ይታወሳል።