ነዋሪዎቹ “እኛ የፖለቲካ ሰዎች አይደለንም፤ ገበሬዎች ነን ፤ መንግስት ለምን አይደርስልንም?” ብለዋል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ ትናንትና ምሽት 3 ሰዓት ላይ በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የአካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ነዋሪዎቹ አሁን ላይ አስክሬኖች በየቦታው ተጥለው መገኘታቸውን ገልጸው ቁጥሩ ምን ያህል ነው የሚለውን ለመግለጽ አስቸጋሪ እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ሕጻናትና ሴቶች አሁን ላይ ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ጫካዎች መግባታቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ መንግስት የማይደርስላቸው ከሆነ አሁንም ሌላ ግድያ ሊኖር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች በቦታው አለመድረሳቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ አስክሬኖች የተጣሉበት ቦታ ጋሪ የማይገባበት በመሆኑ ለማንሳት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እነዚህ ነዋሪዎች “እኛ የፖለቲካ ሰዎች አይደለንም፤ ገበሬዎች ነን ፤ መንግስት ለምን አይደርስልንም? ” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በደረባ (በከብት ማደለቢያና መጠበቂያ ቦታ) ላይ ብቻ 20 አስክሬኖች መገኘታቸውን ያነሱት ነዋሪዎቹ አሁንም ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በአካባቢው በርካታ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት እንዳሉ የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ “መከላከያ ወይም ፌዴራል ፖሊስ ካልገባ ልዩ ኃይሉ ከሞት ያስጥለናል ብለን አናስብም ” ብለዋል፡፡ በስልካቸው ፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስል አንስተው እንዳይልኩ ስልካቸውን መቀማታቸውን የገለጹት የቦኒ ቀበሌ ነዋሪዎች፤ አሁን የያዙት ስልክ ተለዋጭ እና የቤተሰባቸውን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግድያ የተፈጸመባቸው ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ መሆኑንም ነው አል ዐይን አማርኛ ያስታወቁት፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡ ጥቃት ከፈጸመው ኃይል አባላት መካከል በተወሰኑት ላይ እርምጃ መውሰዱንም ክልሉ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡