በምስራቅ ወለጋ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከ150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተረድቻለው- ኢሰመኮ
”ኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች ነሃሴ 12 2013 ዓ.ም ጥቃቱን መፈፀማቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳቱን አስታውቋል
በምስራቅ ወለጋ የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ሊጠናከር ይገባል ብሏል ኢሰመኮ
በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ጊዳ ኪራሙ ወረዳ የ”ኦነግ ሸኔ” ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ማድረሳቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ
ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት ከ150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች ሰዎች አስረድተውኛል ብሏል።
ነሃሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን የ”ኦነግ ሸኔ” ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ማድረሳቸው እና ሁኔታው በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም ኮሚሽ ኑ ገልጿል።
ኮሚሽኑ በመግለጫው አክሎም በታጣቂዎች ጥቃት የተነሳ ሌላው የወረዳው ነዋሪዎች፣ በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውንና በቀጣይ ቀናት ከነዋሪዎች የተውጣጡ ሰዎች ብሔርን መሰረት ያደረገ የአጸፋ ጥቃት በማድረሳቸው 60 ሰዎች መገደላቸውን፤ ነዋሪዎችም ወደ አማራ ክልልና ወደ ኪራሙ ከተማ መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ ተረድቻለሁ ብሏል።
በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ወደ አከባቢው በመመለሳቸው ጊዳ ኪራሙ ወረዳ የተረጋጋ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዱ ቢሆንም በጊዳ ኪራሙና በሌሎች አጎራባች ወረዳዎች አሁንም ድረስ የፀጥታ ስጋት እንዳለም ነው ኢሰመኮ ያስታወቀው።
የአካባቢው ፀጥታ የደረሰበት አስጊ ደረጃ ወደ አጎራባች አካባቢዎች እንዳይዛመትና የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያደርስ አስቸኳይ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑንም ኮሚሽኑ አሳስቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በቀዳሚነት የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር እንዲቀናጁና የአካባቢውን ነዋሪዎች ደኅንነት እንዲያረጋግጡ እንዲሁም የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለጥቃቱ መፈፀም ክፍተት የፈጠረው የፀጥታ ሀይሎች ከአከባቢው መውጣት ምክንያቱን እንዲያጣሩ በአጽንዖት ጥሪ አቅርበዋል።
“በተለይም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪት እና እንቅስቃሴ የተመለከተ አሰራር ተገቢው ምርመራ ሊደረግበት ይገባል” ብለዋል።