በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሁለት ወረዳዎች የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናገሩ
ጥቃቱ በቀወት እና ጣርማበር ወረዳዎች የተፈጸመ ሲሆን ንጹሀን ዜጎች ተገድለዋል ተብሏል
ሁለቱም የድሮን ጥቃቶች በትምህርት ቤቶች ላይ ተፈጽመዋል የተባለ ሲሆን መምህር የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሁለት ወረዳዎች የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
አንድ ዓመት ባስቆጠረው የአማራ ክልል የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት መቋጫ አላገኘም፡፡
በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ተሬ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጉሎ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ለደህንነቱ በመፍራት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የተሬ ቀበሌ ነዋሪ እንዳለው “ትናንት ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 ላይ በመንደራችን ከባድ ፍንዳታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እኔን ጨምሮ የሰፈራችን ነዋሪዎች ፍንዳታው ወደ ተሰማበት ስፍራ ስንሄድ ጥቃቱ ጉሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ እንደተፈጸመ አየን” ሲል ተናግሯል፡፡
አስተያየት ሰጪው አክሎም “በዚህ የድሮን ጥቃት ሶስት አርሶ አደሮች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ትኖር የነበረች ሴት መምህር ከባድ ጉዳት ደርሶባት ወደ ሆስፒታል ተልካለች” ሲልም አክሏል፡፡
“አንድ ሌላ አርሶ አደር በተመሳሳይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል መወሰዱን አውቃለሁ” ያለን ይህ የአይን እማኝ አንድ አርሶ አደር ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰበትም ተናግሯል፡፡
በአካባቢው በመንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ከተጀመረ አንድ ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት እኝህ ነዋሪ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ ንጹሃን ሰዎችን ፋኖን ትረዳላችሁ እያሉ ወጣቶችን ይገድላሉ ብሏል፡፡
በዚህ ምክንያት የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መጡ ሲባል በተለይም ወጣቶች ወደ ጫካ እንደሚሄዱ እና እንደሚደበቁም ይህ አስተያየት ሰጪ ተናግሯል፡፡
በተመሳሳይ በዞኑ በጣርማበር ወረዳ በሚገኘው የመዘዞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የድሮን ጥቃት መፈሙን ስማቸውን እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል።
ነዋሪው እንደገለጹት በዚህ የድሮን ጥቃት በሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
ጥቃቱ ዛሬ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰአት ላይ መድረሱን የገለጹት እኝህ ነዋሪ በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያ ሲገቡ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተፈጸሙ ስለተባሉ የድሮን ጥቃቶች ያለውን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ላሉት ጦርነቶች ለምን ትኩረት ነፈጉ?
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሼ አደራጃለሁ" የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ሶስት ሳምንታት ቀርቶታል።
በአማራ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ምዕራባዊያን ሀገራት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት እና ሀገራት የድሮን ጥቃቶች እንዲቆሙ ንጹሃን ዜጎችም ከጥቃት እንዲጠበቁ ቢጠይቁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የድሮን ጥቃቱ እንደሚቀጥል እና ኢላማውን የጠበቀ ጥቃት ማድረሳችንን እንቀጥላለን ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡