አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ላሉት ጦርነቶች ለምን ትኩረት ነፈጉ?
ተመድን ጨምሮ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በትግራይ የተለየ ፍላጎት አላቸው?
የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ አሁንም የተለየ አቋም እንደሌላቸው ተናግረዋል
በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደው እና ለሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ በተፈረመ የሰላም ስምምነት መቆሙ ይታወሳል፡፡
ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም የተካሄደው ይህ ጦርነት ተፋላሚዎች ወደ ተኩስ አቁም እንዲሄዱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት ቡድን ሰባት፣ ብሪታንያ እና ሌሎችም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት በጋራ እና በተናጠል የተለያዩ ጫናዎችን ሲያደርጉ ነበር፡፡
ጦርነቱ በፍጥነት ባለመቆሙ ምክንያትም ሀገራት በኢትዮጵያ ያላቸውን ፕሮግራሞች ማቋረጥ፣ ቢሮ መዝጋት፣ እንደ አግዋ አይነት ለኢትዮጵያ ተሰጥተው የነበሩ የገበያ እድሎችን ማቆም፣ ተፈቅደው የነበሩ ብድሮችን መከልከል እና የቀጥታ በጀት ድጋፎችን ማቋረጥ በኢትዮጵያ ላይ ከተደረጉ ጫናዎች ዋነኞቹ ነበሩ፡፡
እንዲሁም የጸጥታው ምክር ቤት እና የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ተከታታይ የሆኑ ውይይቶችን ማድረግ እና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሪፖርቶችን ከማውጣት ጀምሮ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረትም ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በቆመ በተወሰኑ ወራት ውስጥ የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ በሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ በአማራ ክልል ሌላ ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡
በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአራት ወራት ተራዘመ
አንድ ዓመት በሞላው በዚህ ጦርነት ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች፣ የጅምላ እስሮች እና ከህግ ውጪ ግድያዎች እየተፈጸሙ እንደሆነ ተመድን ጨምሮ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ሪፖርት ያስረዳሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልልም በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ታጣቂዎች መካከል በሚደረጉ ግጭት ዜጎች ለእገታ፣ ግድያ እና ማንነቶችን መሰረት ላደረጉ ጥቃቶች እንደተጋለጡ በተለያዩ ጊዜያት እነዚሁ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አጋር የሚባሉት እነዚህ ተቋማት እና ሀገራት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት እንዲቆም ሲያደርጉት የነበረውን ጫና ለምን አሁን ሰፊ ህዝብ እና አካባቢ በሚሸፍኑት የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ መድገም አልቻሉም የሚል ጥያቄ ይነሳባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት እና ንግድ አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም እና አለመረጋጋቶች እንዲፈቱ ሳደርገው የነበረው አቋም አልተቀየረም ብሏል፡፡
በህብረቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሮላንድ ካቢያ ከየትኛውም የአዲስ አበባ አጋር በላይ በኢትዮጵያ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ግጭቶች እንዲቆሙ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ለአይ ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ በቅርቡ አባል የተቀላቀለችው ብሪክስ እንደ በተቋምም ሆነ በተናጥል የንጹሃን ግድያዎች እንዲቆሙ እና የፖለቲካ ውጥረቶች እንዲረግቡ አንድም ቀን አውግዘው አያውቁም ሲልም አምባሳደር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም በጽኑ ስንጠይቅ ነበር፣ በሰላም ስምምነቱ ውይይት ላይ ባንጋበዝም የተፈረመው ሰምምነት እንዲተገበር የሚጠበቅብንን እያገዝን ነው የሚሉት አምባሳደሩ አሁንም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ባሉ ግጭቶች ምክንያት ንጹሃን ከጥቃት እንዲጠበቁ፣ ተፋላሚዎችም ወደ ውይይት እንዲመጡ ግፊት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ የኢትዮጵያ አጋር አሜሪካ ስትሆን በአማራ ክልል ያለው ውጊያ እንደሚያሳስባት አስታውቃለች፡፡
በአዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ ለአል ዐይን በሰጠው ምላሽ “በአማራ ክልል ያለው ውጊያ ያሳስበናል፣ ተፋላሚዎች ንጹሃን ዜጎችን ከአደጋ መጠበቅ እና የሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ አለባቸው “ ብሏል፡፡
ኢምባሲው አክሎም በክልሉ ላለው ውጊያ መፍትሄው ውይይት ነው ብሎ እንደሚያምን የገለጸ ሲሆን በኦሮሚያም ያለው የንጹሃን ሞት፣ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንደሚያሳስበውም አስታውቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት እና ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ሲደረግ የቆየው ድርድር ዳግም እንዲቀጥልም ኢምባሲው አሳስቧል፡፡
ይሁንና አሜሪካ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ስታደርገው የነበረውን ያህል ለምን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ግጭት እንዲቆም ከመግለጫ ማውጣት እና ጥቃቶችን ከማውገዝ ያለፈ ጫና ማድረግ አልቻለችም? በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ኢምባሲው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የኢትዮጵያ አጋር የሆኑ ሀገራት እና ተቋማት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ሲያደርጉት የነበረው ጫና አሁን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ካሉት ችግሮች ጋር አነጻጽረው እንዲነግሩን ጠይቀናቸዋል፡፡
ፕሮፌሰር መረራም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እና የአሁኑ የአማራ እና ኦሮሚያ የፖለቲካ ችግሮች የተለያዩ መልኮች ያሏቸው እና የማይነጻጸሩ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡
"አሁን ላይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ግጭቶች እና ጦርነት የስልጣን ጥያቄዎች ናቸው፣ እንደ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ያሉት ሀገራትም በፌደራል መንግስት ላይ ጫና መፍጠር ያልቻሉት ለዚህ ነው" ሲሉም አክለዋል ፕሮፌሰር መረራ፡፡
ደስታ ጥላሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ሲሆኑ ተመድን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች ሀገራት እና ተቋማት በሁለቱ ክልሎች ላሉት ችግሮች ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጡ እና ጫናም እየፈጠሩ እንዳልሆነ እረዳለሁ አይደለም ብለዋል፡፡
"እነዚህ ሀገራት እና ተቋማት እንደ ከዚህ በፊቱ ጦርነት እንዲቆም ጫና የማይፈጥሩት ከጀርባቸው የራሳቸው ጥቅም በመኖሩ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ዋና ጸሀፊዋ ተናግረዋል፡፡
"በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ሕወሃት ለዓመታት በስልጣን ላይ መቆየቱ፣ አሁንም በቀጣይ ጥቅማችንን ያስከብርልናል ብለው ማመናቸው፣ ብዙ ወዳጆችን ያፈራ እና ህጋዊ ተቋም ሆኖ መቆየቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት እና ተቋማት ጦርነቱ እንዲቆም በፌደራል መንግስት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ምክንያቶች ናቸው" ብለዋል፡፡
ዋና ጸሃፊዋ እንዳሉት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታትን ከመሰረቱ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ኢትዮጵያዊያን በጦርነት እና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲጎዱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመጡ መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ግፊት እያደረገ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡
"ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት እና ተቋማት ንጹሃን ዜጎች በጦርነቶች እና ግጭቶች ቢጎዱ ምንም አይመስላቸውም" ያሉት ደስታ ጥላሁን ዋናው ትኩረታቸው ጥቅማቸው መከበሩ እንጂ የጦርነቱ ሂደት እና ጉዳት እንደማያሳስባቸውም ተናግረዋል፡፡
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ጦርነቶች እና የፖለቲካ ችግሮች በተራዘሙ ቁጥር ንጹሃንን ከመጉዳቱ ባለፈ ተሳታፊዎች እና የውጭ ጣልቃ ገብነቶች እየበዙ እና ጉዳዩም የበለጠ እየተወሳሰበ ስለሚሄድ ተፋላሚዎች ችግሮቻቸውን በውይይት ሊፈቱ ይገባል ብለዋል ዋና ጸኃፊዋ፡፡