በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን መገደላቸውን ኢሰመጉ ገለጸ
በክልሉ በቀጠለው ግጭት ከባድ መሳሪያዎች በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኝ በሪፖርቱ አመላክቷል
በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ቀጥለዋልም ነው የተባለው
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜ በሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሱ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታወቀ፡፡
ጉባኤው በአማራ ኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኝውን ሁኔታ ባወጣበት ሪፖርቱ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ባለመወጣታቸው የመብት ጥሰቱ እንደቀጠለ ይገኛል ብሏል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ ከፍተኛ የጦር መሳርያዎችን ጭምር በመጠቀም የሚካሄደው ግጭት ቀጥሏል ያለው ጉባኤው በዚህም የሰዎች ህይወት እያለፈ፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ግጭቱ በንፁሃን ላይ እያደረሰ ከሚገኘው ሞትና የአካል ጉዳት ባለፈ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ የጤናና የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
ከዚህ ባለፈም በድሮን የሚፈጸሙ ጥቃቶች የንጹሀን ህይወት አደጋ ውስጥ መክተታቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ በመስከረም እና ጥቅምት ወራት በአዊ ብሄረሰብ ዞን፣ በሰሜን ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ እንዲሁም በዳንግላ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ ት/ቤቶች ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ንጹሃን ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት እንደደረሰ ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ አሮጌ ገበያ፣ ምስራቅ ጎጃም ሞጣ አስተርዮ ተብሎ በሚጠራ የገጠር ቀበሌ እንዲሁም ምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ፈረስ ቤት ከተማ የደረሱ የድሮን ጥቃቶች ሞትና የአካል ጉዳት አስከትለዋል፡፡
በሌላ በኩል በምስራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ እሮብ ገበያ ከተማ መስከረም ወር በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ሁለት መምህራን መገደላቸውን እንዲሁም በተደጋጋሚ በሚፈጸሙት የቦምብ ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል ብሏል ኢሰመጉ፡፡
በዚህም ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከክልልና ከአንዳንድ የዞን ከተሞች ውጪ የትምህርት ሂደቱ በመቋረጡ በተማሪዎች፣ በወላጆች፣ እንዲሁም በማህበረሰቡ ላይ ማህበራዊ እና ስነልቦናዊና ጫናዎችን መፍጠሩ ተሰምቷል፡፡
በአማራ ክልል በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ያለምንም የመያዣ ትዕዛዝ ተይዘው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በወታደራዊ ካምፕና በተለያዩ ማቆያዎች ውስጥ መሆናቸውንና ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
ኦሮሚያ ክልልን በተመለከተ በተለይም በምስራቅ ወለጋ ዞን ሰላሙ ወደ ነበረበት ባለመመለሱ በስቡ ስሬ ወረዳ ቀበሌዎች ፣በኑኑ ወረዳ ቀበሌዎች ፣በጂማ አርጆ ወረዳ ቀበሌዎች እና በኪረሙ ወረዳ ቀበሌዎች በሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ግድያ፣ የአካል ጎዳት ፣ አስገድዶ መሰወር እና የንብረት ውድመት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት እየተፈጸመ ነው ተብሏል፡፡
በምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ መስከረም 9/2017ዓ.ም በአካባቢው ሽማግሌዎች ውሳኔ ተሰጥቶኝ ነው በሚል ባለቤቱን ግንድ ላይ አስሮ በመግረፍ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰባት እና ይህ የሰብአዊ መብት መርሆችን እንደሚጥስ ጉባኤው ገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በድራሼ ዞን፣በኮንሶ ዞን እና በአማሮ ኬሌ ዞኖች በ2016 ዓ.ም መጨረሻ ግድያ፣ እስራት፣አስገድዶ መሰወር፣ ንብረት ውድመት እና ከስራ ማፈናቀል መፈጸሙን ኢሰማጉ ስለማረጋገጡ ጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ወደ አካባቢው በመግባት 4 ሰዎች ላይ የሞት እና 1 ሰው ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፡፡
የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል ያለውን የትጥቅ ግጭት በሰላም የሚፈታበትን ሁኔታ በማመቻቸት በክልሉ እየተፈጠሩ ያሉትን ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያስቆም፣
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ታስረው ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችን የሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡ እና ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እንዲያከብሩና እንዲያስከብር ፤በኦሮምያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጸሙት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ኃላፊነት የሚወስዱትን ባለድርሻ አካላት የክልሉ መንግስት በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡
ከሳምንታት በፊት መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ላይ በአዲስ መልክ እርምጃ እንደሚወስድ ማሳወቁን ተከትሎ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ግጭቶች ተባብሰዋል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ መንግስት በክልሉ መምህራንን ጨምሮ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ያለአግባብ በጅምላ እያሰራ መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርቱ ማሳወቁ ይታወሳል።