አሜሪካ፤ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው ’የጋዜጠኞች እና አንቂዎች ጅምላ እስር‘ ጉዳይ እንዳሳሰባት ገለጸች
ዋሽንግተን በኤምባሲዋ በኩል መግለጫ አውጥታለች
አሜሪካ ተገቢው የህግ ሂደት እንዲጠበቅና የህግ የበላይነት እንዲከበር ጥሪ አቅርባለች
አሜሪካ፤ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የጋዜጠኞች እና የማህበረሰብ አንቂዎች ጅምላ እስር ጉዳይ እንዳሳሰባት ገለጸች፡፡
አሜሪካ አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ባወጣችው መግለጫ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የጅምላ እስር ጉዳይ እንዳሳሰባት አስታውቃለች፡፡
በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና የማህበረሰብ አንቂዎች በጅምላ እየታሰሩ ነው ያለው ኤምባሲው የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ሀይሎች ተገቢውን የህግ ሂደት እንዲጠብቁና የህግ የበላይነት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጉዳዩን በተመለከተ የገለጸውን ስጋት እንደሚጋራውም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው፡፡
ሆኖም ኤምባሲው ታሰሩ ያላቸው ጋዜጠኞች እና ማህበረሰብ አንቂዎች እነማን እንደሆኑ በስም አልጠቀሰም፡፡
የአማራ ክልል እያካሄድኩ ነው ባለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ንስር እና አሻራ የተባሉ የዲጂታል (ዩቲዩብ) ሚዲያዎች ዘጋቢዎችና የስታፍ አባላትን ጨምሮ ዘጠኝ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ሮይተርስን መሰል የውጭ የሚዲያ ተቋማት ዘግበዋል፡፡
በምትሰጣቸው ፖለቲካ አዘል አስተያየቶች የምትታወቀው መምህርት መስከረም አበራ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ/ም የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርባ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የ13 ቀናት የምርመራ ጊዜ መፍቀዱ ይታወሳል።
የአብን የፓርላማ አባላት በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ነው ያሉት "መንግስታዊ እገታና ስወራ" በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቁ
የአማራ ክልል ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ ሰላምና ደህንነት ቢሮ የክልሉን ወቅታዊ ኹኔታ አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫ በክልሉ ባደረገው ህግ የማስከበር ስራ ከአራት ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል።
የቢሮው ኀላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዳሉት በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 4 ሺህ 552 ግለሠቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ40 በላይ የሚኾኑት በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው የነበሩ እንደኾኑ ጠቁመው፤ 210ሩ በነፍስ ግድያ የተጠረጠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ሕገ ወጦችን ለመያዝ ከሚደረግ ሥራ ውጭ ክልሉ አስተማማኝ ሰላም ላይ እንደሚገኝም ነው አቶ ደሳለኝ የተናገሩት፡፡ የክልሉን ዘላቂ ሰላም የማስጠበቁን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡
ትክክለኛውን የፋኖ ስም የማይወክሉ፣ በፋኖ ስም ተደራጅተው በሕዝብ ላይ የተለያዩ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እንደማይታገስ ኃላፊው አስቀምጠዋል።