በአማራ ክልል የቀጠለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዴት ሊቆም ይችላል?
በአማራ ክልል በመንግስት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ጦርነት 17ኛ ወሩን ይዟል
በክልሉ እየተደረገ ያለው ጦርነት ተጽዕኖ ከሀገር አልፎ የጎረቤት ሀገራትን ሊጎዳ የሚችል ነው ተብሏል
በአማራ ክልል የቀጠለው የሰው እና ቁሳዊ ውድመት እንዴት ሊቆም ይችላል?
ሚያዚያ 2015 ዓ.ም የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም አደራጃለሁ የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል በመንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
ይህ ጦርነት ቶሎ ሊቆም እንደሚችል ተገምቶ የነበረ ቢሆንም 17ኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን ተፋላሚዎችን ወደ ሰላም እንዲመጡ የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡
አል-ዐይን አማርኛ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዴት ሊቆም ይችላል? ሲል ምሁራንን አነጋግሯል፡፡
በባርዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ያየሁ ገነት እንዳሉት በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከክልሉ ባለፈ በሀገር እና በምስራቅ አፍሪካ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ነው ብለዋል፡፡
ጦርነቱ ያደረሰው ጉዳት መጠን በሚገባ ተጠንቷል ብዬ አላስብም የሚሉት መምህሩ ጦርነቱ ለንጹሃን ህይወት መጥፋት ከመሆኑ በተጨማሪም ከባድ የቁስ እና የሰብዓዊ ውድመት እያደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ፖለቲካ እና ሌሎች ክስተቶች ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ክልል መሆኑን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ያየሁ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ጉዳቱም ቀላል ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
“ጦርነቱን በመሸሽ ሰዎች ከወረዳ ከተሞች ወደ ዞን ከተሞች እየተፈናቀሉ ናቸው፣የክልሉ ነዋሪዎች የተሻለ ደህንነት ፍለጋ ወደ አጎራባች ክልሎች እና ሀገራት እየተሰደዱ ናቸው፣ ይህ ደግሞ የራሱ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ቀውስ የመፍጠር እድሉ ሰፊ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“ጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን አለመረጋጋት እንደ ጥሩ እድል እና ስጋት መመልከታቸው አይቀሬ ነው” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ያየሁ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ሀገራት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ አልያም ስጋታቸውን ለመቆጣጠር ሲሉ በኢትዮጵያ ላይ የራሳቸውን አቋም ሊያዙ ይችላሉ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አደጋ ነው ብለዋል፡፡
መምህሩ አክለውም ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ህዝቡ በጦርነቱ ምክንያት እየከፈለ ያለውን ዋጋ አልተረዱም፣ ለመደራደር ፈቃደኛ እንደሆኑ ቢናገሩም ሰላም እንዲመጣ ፍላጎት ያላቸውም አይመስልም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“በዚህ ጦርነት የሚያሸንፍ አካል አይኖርም” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ያየሁ ሰላም የሚመጣው በእውነተኛ ድርድር እና ህዝብ እየደረሰበት ያለውን ውድመት ሲረዱ ብቻ ነው”ም ብለዋል፡፡
ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ምክንያቶች መከፋፈላቸው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ዲፕሎማቶች እና ሚዲያዎች በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ውድመት በልኩ እንዳይረዱት አድርጓል ብለው እንደሚያምኑም ረዳት ፕሮፌሰር ያየህ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ሰለሞን መብሬ በበኩላቸው በአማራ ክልል ያለው ጦርነት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
“ይህ አውዳሚ ጦርነት እያደረሰ ያለውን ጉዳት የማያውቅ አለ ብዬ አላስብም” የሚሉት ዶክተር ሰለሞን “ጦርነቱ መቆም የሚችለው በተፋላሚዎቹ መልካም ፈቃድ ብቻ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ይደረግ ሲባል ቆይቷል፣ ተፋላሚዎች ለጥቅሙ ቆመንለታል ለሚሉት ህዝብ እውነተኛን ነገር ማድረግ ከፈለጉ ጦርነቱ ይቆማል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል ዶክተር ሰለሞን፡፡
ሁለቱ ዋነኛ የጦርነቱ ተፋላሚዎች ሰላም ለማምጣት የሚሄዱበት ርቀት ዋነኛው የጦርነቱ ማቆሚያ መንገድ እንደሚሆንም ዶክተር ሰለሞን ጠቅሰዋል፡፡
በአማራ ክልል ከተሞች ሰዎች በገፍ እየታሰሩ መሆኑ ተገለጸ
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዋነኛ ተፋላሚዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በተቋቋመው የሰላም ምክር ቤት ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ በበኩላቸው በአማራ ክልል እየደረሰ ያለውን ውድመት በሚገባ የተረዳው አካል የለም ብለዋል፡፡
“የፖለቲካ ፍላጎቶች ለጦርነቱ መነሻ እና ለጦርነቱ አለመቆም ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብዬ አምናለሁ” የሚሉት አቶ እያቸው መንግስትም ሆነ የፋኖ ታጣቂዎች የህዝቡን ጉዳት እንዳልተረዱትም ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ እያደረሰ ያለውን ከባድ ውድመት ዲፕሎማቶች እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እንዲረዳው እና ተፋላሚዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ግፊት እንዲያደርጉ የሰላም ምክር ቤቱ እየጣረ እንደሆነም አቶ እያቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ካሳለፍነው ሰኔ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቱን ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ኢሰመኮ በዚህ የአራት ወራት ሪፖርቱ በአማራ ክልል በመንግስት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ከ160 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን ገልጾ ተፋላሚዎች ንጹሃንን ከጥቃት እንዲጠብቁ እና ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሲልም አሳስቧል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል መንግስት ኮሙንኬሽን ከሰሞኑ በጋራ በሰጡት መግለጫ በክልሉ "ህግ የማስከበር" ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸው ይታወሳል፡፡