በሕፃን ሔቨን ጉዳይ የተጀመረው የሚዲያ ዘመቻ እንዲቆም የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ጠየቀ
ማህበሩ እንዳለው የወንጀል ክርክር ሂደቱ ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ የሚዲያ ዘመቻው የዳኝነት ነጻነትን የሚጋፋ ነው ብሏል
የ7 ዓመቷ ህጻን ሔቨን ከአንድ ዓመት በፊት በባህርዳር በተፈጸመባት የአስገድዶ መደፈር ህይወቷ አልፏል ተብሏል
በሕፃን ሔቨን ጉዳይ የተጀመረው የሚዲያ ዘመቻ እንዲቆም የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ጠየቀ፡፡
ከሰሞኑ የአማራ ክልል መዲና በሆነችው ባህር ዳር ከተማ የሰባት ዓመት እድሜ ያላት ህጻን ሔቨን የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ከተፈጸመባት በኋላ ህይወቷ እንዳለፈ የህጻኗ እናት ለተለያዩ ሚዲያዎች ተናግራለች፡፡
በርካቶችን ያስቆጣው ይህ ድርጊት ወንጀሉን ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ በተፋጠነ ምርመራ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የ25 ዓመት እስር እንደተላለፈበትም ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎ ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ ላይ የተላለፈበት ውሳኔ በቂ ካለመሆኑ በላይ ግለሰቡ ፍርዱ እንዲቀነስለት ይግባኝ ማለቱም ተነስቷል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም እንደተፈጸመ የተገለጸው ይህ ወንጀል ጉዳዩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ሲሆን ተቋማት ሳይቀር በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ናቸው፡፡
በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ህፃን ሄቨንን ጉዳይ እንደሚከታል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው በሕፃን ሔቨን ላይ በተፈጸመው ዘግናኝ ወንጀል ማዘኑን ገልጾ ድርጊቱም ከሃይማኖትና ከባሕል ያፈነገጠ በመሆኑ በጥብቅ አወግዛለሁ ብሏል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ወንጀል እና ወንጀለኛ የሚዳኝበት ሕግና ስርዓት እያለ እና ጉዳዩም በዳኝነት አካሉ በይግባኝ እየታየ ባለበት ሁኔታ የዳኝነት ነጻነት እና የሕግ የበላይነት መርህን የሚጥስ የሚዲያ ዘመቻ መደረጉ ስህተት መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ በማህበራዊ ሚዲያው ቅጣት አንሷል፣ ተከሳሹ ይግባኝ ሊጠይቅበት አይገባም እና መሰል ነገሮችን በማናፈስ ዳኞች ህግና ማስረጃን ብቻ መሰረት አድርገዉ በነፃነት እንዳይሰሩ ያልተገባ ጫናን የሚፈጥር ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን ማህበሩ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
እንደ ማህበሩ መግለጫ የሕግ የበላይነት መከበር የሚጠቅመው በቅድሚያ ለራስ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲዳኙ መፍቀድ ተገቢ ነዉም ብሏል ማህበሩ፡፡
ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸዉ ዉሳኔዎች ስህተት አለባቸዉ ቢባል እንኳ በተቀመጠዉ የይግባኝ ስርዓት መሰረት ከሚታረሙ በስተቀር ማንኛዉም የመንግስት አካልም ሆነ ግለሰብ ውሳኔውን ከሰጠውም ሆነ ጉዳዩ በይግባኝ ከቀረበለት ፍርድ ቤትን መተቸት እንደማይገባም አስታውቋል፡፡
ተከሳሹ ይግባኝ ማቅረብ የለበትም የሚለው ዘመቻ የአገሪቷን በሕግ የመዳኘት መብትን አደጋ ላይ የሚጥል እና በይግባኝ የሚመለከተዉ ፍርድ ቤት ላይ ያልተገባ ጫና በማሳደር የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት የሚጥስ በመሆኑ የሚዲያ ዘመቻው እንዲቆም ጠይቋል፡፡
ማህበሩ የትኛዉም ፍትህ ፈላጊ አካል ነፃና ገለልተኛ በሆነ የዳኝነት አካል ፊት ቀርቦ እንዲዳኝ እና ዳኞችም ህግንና በማስረጃን ብቻ መሰረት አድርገዉ በነፃነት እንዲወስኑ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲከበር እንሚሰራ ገልጿል፡፡