ከመሥራች አባላት ሥም ዝርዝር ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ቅንጅት ክስ ተመስርቶበታል
የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የመሥራች አባላት ጉዳይን አስመልክቶ ፓርቲው ያቀረበው የመሥራች አባላት ዝርዝር ላይ ቦርዱ 50 የሚሆን ናሙና በመውሰድ ያደረገው ማጣራት ስለ ትክክለኛነቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባው በመሆኑ፤ ቦርዱ ጉዳዩን ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ልኮት እንደነበር ይታወሳል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም ባደረገው የማጣራት ሥራ ከሶማሌ ክልል 1145 መሥራች አባላት፣ ከአፋር ክልል 72 መሥራች አባላት፣ ከኦሮሚያ ክልል 23 መሥራች አባላት፣ ከአ.አ. ከተማ አስተዳደር 58 መሥራች አባላት በጠቅላላው የ1298 መሥራች አባላት በተጠቀሱት አድራሻ ያለመኖራቸውን ማረጋገጡን የሚያስረዳ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ይህም የቦርዱም ሆነ የፖሊስ ኮሚሽኑ የማጣራት ሥራ የሚያሳየው ፓርቲው እያወቀ ወይም ማወቅ እየተገባው ፣ በቃለመኃላ በተረጋገጠ ሰነድ ያቀረበው የመሥራች አባላት ሥም ዝርዝር በተጭበረበረ ተግባር የፓርቲውን የዳግም ምዝገባውን ሂደት ማስፈጸም መፈለጉን እንደሆነ መረዳቱን ቦርዱ ገልጿል፡፡
ስለዚህ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 98/1/ /ሠ/ መሠረት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲሰረዝ ተወስኗል ይላል ቦርዱ ያወጣው መግለጫ፡፡ በዚህ ጉዳይም በአቃቤ ሕግ በኩል ክስ ተመስርቶበት እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
አፈጻጸሙ በተጀመረው የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ መሳተፍ የሚችሉት ፓርቲዎች በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉት 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለመሆናቸውም ነውቦርዱ ያሳወቀው። ለመሳተፍ ቅቡልነት ያላቸው እስከአሁን ያለውን ሂደት አጠናቀው የጨረሱ ፓርቲዎች መሆናቸውንም ነው የቦርዱ መግለጫ የሚያሳየው፡፡