ፓርቲው ተጨማሪ አባላትን አስፈርሞ ባቀረበው ሰነድ ላይ ያልተሟሉ እና የጎደሉ ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ቦርዱ አስታውቋል
ፖሊስ ቅንጅት ያቀረበውን የአባላት ዝርዝር እንዲያጣራለት ምርጫ ቦርድ ጠየቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ( ቅንጅት) መስራች አባላት ስም ዝርዝርን እንዲያጣራለት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥያቄ አቀረበ፡፡
ፓርቲው በተጠየቀው መሰረት ከ8 ክልሎች የተሰበሰበ የ7 ሺ 214 የመስራች አባላት ፊርማ የያዘ ሰነድ ማቅረቡን ያስታወቀው ቦርዱ ባደረገው ማጣራት ጎድለው ያገኛቸውና ያልተሟሉ ብዙ ነገሮች በመኖራቸው የመስራች አባላቱን ስምና ፊርማ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አለመቻሉን አስታውቋል፡፡
ጥሪ ካደረገላቸው 50 ፈራሚዎች መካከል፣ አንዱ ብቻ መፈረሙን፣በማመልከቻና በቃለ መሃላ ቅጽ ላይ የፊርማ መለያየት መኖሩን፣ አባልነታቸውን አሟልተው ስለለመዝገባቸው በፊርማቸው ያላረጋገጡ እንዲሁም እድሜ፣ ጾታ፣ የምዝገባ ቀናቸው የማይታወቅ ፈራሚ ስሞች በሰነዱ ማግኘቱንም ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን ተመልክቶ ህጋዊ ማጣራት እንዲያደርግለት በዛሬው እለት የካቲት 27 ቀን 2012 ዓ.ም አስተላልፏል፡፡
ቦርዱ እንዳስቀመጠውም ከሆነ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው አዋጅ መሰረት በአባልነት ያልተመዘገበን ሰው የተመዘገበ በማስመሰል የሌለን ሰው እንዳለ ማስመሰል ሃሰተኛ ስምና ፊርማ ማዘጋጀት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
በአዋጁ መሰረት ቦርዱ ሊወስድ ከሚችላቸው ምዝገባን ከመከልከልና ከማገድ በተጨማሪ አግባብ ባለው የወንጀል ህግ መሰረትም ሊጠየቅ እንደሚችል የህጉ ድንጋጌዎች ያዛሉ፡፡