ብሄረዊ ባንክ የንግድ ባንክንና የደንበኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት በጊዜያዊነት መቋረጥን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባጋጠመው የቴክኒክ ወይም የሲስተም ችግር ምክንያት ባሳለፍነው አርብ ሌሊት ላይ የሲስተም መቋረጥ አጋጥሞት እንደነበረ መግለጹ ይታወሳል።
ባንኩ ትናንት በሰጠው መግለጫ መጀሪያ ላይ የመደበኛ የባንክ ስርዓቱ መመለሱን በኋላ ላይ የኤቲኤም እና የሞባይል በባንኪን አገልግሎቶቹ በቅደም ተከተል መሰረት መመለሳቸውን አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፤” ባንኮች በስርዓቶቻቸዉ ላይ በየጊዜዉ የደህንነት ፍተሻ እንዲሁም የማሻሻያ ሥራዎችን ያከናዉናሉ፤ በዚህ ወቅት የባንኮች አገልግሎት አልፎ አልፎ ሊቋረጥ ይችላል”
“በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችያለሁ” ብሏል።
ብሄረዊ ባንክ ችግሩ ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የባንኩን እና የደንበኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውቋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ባንኩ በመደበኛነት በሥርዓቶቹ ላይ በሚያደርገዉ ማሻሻያና ፍተሻ ምክንያት የተከሰተ መሆኑንም ብሄራዊ ባንክ በመግለጫው አረጋግጧል።
የተከሰተው ችግርም የባንኩን፣ የደንበኞቹን እንዲሁም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አለመሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
በችግሩ ምክንያት የተከሰቱ የደንበኞች መጉላላትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊዉን ምርመራ በማድረግ ወደፊት ለህብረተሰቡ እንደሚያሳውቅም ገልጿል።
ብሄራዊ ባንክ በመግለጫው አክሎም “በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደህንነቸዉ የተጠበቀ በመሆኑ ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም መቀጠል ይችላል” ብሏል።