የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ303 ሚሊየን ዶላር ያስገነባው የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ተመረቀ
ግንባታው ከ5 ዓመት በላይ የወሰደው ህንጻው ከምስራቅ አፍሪካ ረጅሙ መሆኑ ተነግሮለታል
ህንጻ ከመሬት በላይ 209 ነጥብ 15 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፤ ባለ 53 ወለል ነው
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ያስገነባውን ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ በዛሬው እለት አስመረቀ።
አዲሱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው እለት መርቀው ከፍተውታል።
በምረቃው ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ አመራሮች እንዲሆን የባንኩ ደንበኞች መገኘታቸውን ባንኩ አስታውቋል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ከመሬት በላይ 209 ነጥብ 15 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፤ ምድር ውስጥ ያለውን ጨምሮ 53 ወለል ያለው ነው።
በውስጡም የቢሮ አገልግሎት ከሚሰጡ ክፍሎች በተጨማሪ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን፣ ሙዚየም እና ሲኒማ ቤትን ያካተተ ሲሆን፥ እስከ 1 ሺህ 500 መኪናዎችን መያዝ የሚችል ማቆሚያም አለው።
5 አመት ከ11 ወር የወሰደው ግንባታው 303 ሚሊየን 500 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ80 ዓመታት በፊት ማለትም በ1935 ዓ.ም በ1 ሚሊየን ማርያትሬዛ ካፒታል መመስረቱን የባንኩ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ የብሄራዊ ባንክን እና የንግድ ባንክን ሚና ሲወጣ ቆይቶም በ1955 ዓ.ም ለሁለት ተከፍሎ የኢትዮጵያን ገንዘብ ቁጥጥርና የማሳተም ኃላፊነት ለብሄራዊ ባንክ፤ የንግድ ሥራ ዘርፉ ደግሞ ለአሁኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሰጠቱን ባንኩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምስረታው ጀምሮ ለህብረተሰቡ የባንክ አገልግሎትን በማዳረስ፣ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ በሀገሪቱ የሚከናወኑ በርካታ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ጊዜ 824 ቢሊየን ብር የተቀማጭ ገንዘብ እንዲሁም 1.1 ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት ያለው መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስታውቀዋል።
ባንኩ ከ1 ሺህ 800 በላይ ቅርንጫፎች እንዲሁም ከ34 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እንዳሉት አቶ አቤ ገልፀዋል።