የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግጭቶች "በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" እንዲቆሙ ጠየቀ
ኮሚሽኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ "አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ" አቅርቧል
የኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ስራዬን አዳጋች እያደረጉት ነው ብሏል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ "አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ" አቅርቧል።
አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በምክክር ለመፍታት መቋቋሙን ያወሳው ኮሚሽኑ፤ በተለያዩ ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ የኃይል እርምጃዎች ደህንነትንና ህልውናን በመፈታተን ላይ ናቸው ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ወቅት፤ በተለያዩ ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ስራ አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉም ብሎል፡፡
ሰኞ ነሐሴ አንድ፤ 2015 ዓ.ም "ልዩ ስብሰባ" ማድረጉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በዚህም በመላው ሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች "በአስቸኳይ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ" እንዲቆሙ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ ተፋላሚ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን ወይም ጥያቄዎቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ "አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ" አቅርቧል፡፡
ለዚህም ተግባራዊነት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማወያየትና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ ነኝ ብሏል።
በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በበርካታ ከተሞች ግጭት መኖራቸውን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው።
ክልሉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰላሚ እንቅስቃሴ እንዲመለስ አደርጋለሁ ያለው የፌደራል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።