የአማራ ክልል በመደበኛ የጸጥታ ሀይል ሕግ ማስከበር አልችልም በሚል የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ ይታወሳል
መንግስት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ በአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንጂታወጅ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማስክበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ፤ ይህ እንቅስቃሴ የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ በመክቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ገልጿል።
መንግስት ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ሁሉ የሰላም እና ህጋዊ መንገድን እንዲከተሉ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያደርግ እንደቆየም በመግለጫው ላይ ተጠቅሳል።
ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አክሎም የታጠቁ ሀይሎች እየፈፀሙ ባለዉ ጥቃት ምክንያት የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነውም ብሏል፡፡
የክልሉ መንግስትም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ፣ ሁኔታውን በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ፣ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በኢፌድሪ ህገ መንግስት መሰረት እንዲደነግግ እና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ አቅርቧል ተብላል።
በመደበኛ የህግ ስርዓትን መሰረት አድርጎ ይህን ፈር የለቀቀ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አዳጋች ሁኔታ በመፈጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ተገልጻል።
ህገመንግስቱ እና ህገመንግስታዊ ስርዓት ላይ የተቃጣ አደጋን በመደበኛ የህግ ስርዓት ለመቆጣጠር ባልተቻለ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ህገመንግስታዊ ስርዓትን ከአደጋ የመከላከል ስልጣን አለው።
በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በህገመንግስቱ የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ስላለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 እንዲታወጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተገልጿል።
ይሁንና በአማራ ክልል የተወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አልተገለጸም።
በህገ ሙንግስቱ ድንጋጌ መሰረት የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣን ያለው ቢሆንም ውሳኔው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቅ እንዳለበት ያስቀምጣል።