ነዋሪዎች በክልሉ ውስጥ እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች እየተገደሉ እንደሆነ ተገልጿል
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሚያዝያ ወር በክልል ልዩ ሀይሎች ላይ የማፍረስ እና “መልሶ ማደራጀት“ ውሳኔ ካሳለፈበት ጊዜ አንስቶ በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መጥቷል፡፡
የሌሎች ክልሎች ልዩ ሀይሎች ባልፈረሰበት ሁኔታ ለምን አስቀድሞ የአማራ ክልል ይፈርሳል በሚል የተጀመረው ተቃውሞ ቀጥሎም አሁን ላይ ክልሉን በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ማስከበር ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል፡፡
ይህን ተከትሎም አልዐይን አሁናዊ የክልሉ ሁነታ ምን እንደሚመስል ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የጎንደር ከተማ ነዋሪ በጎንደር አዘዞ አካባቢ በፋኖ እና በሀገር መከላከያ ሰራዊት መካከል ከባድ ጦርነት መካሄዱን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል።
ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሀሙስ ለአርብ ሌሊት ሰባት ሰዓት ድረስ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት ሲካሄድ መቆየቱን የሚናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ አሁን ላይ የሞቱ ሰዎች አስከሬን እየተነሳ፣ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ሆስፒታል በመወሰድ ላይ ናቸውም ብሎናል፡፡
አስተያየት ሰጪው አክሎም ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ቁጥር መለየት አይቻልም፣ ከተዋጊዎች በተተኮሰ ጥይት የንጹሃን ሕይወትም እንዳለፈ ተናግሯል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ከዛሬ ረፋድ ጀምሮም ወደ አደባባዮች መውጣት መጀመራቸውን የነገረን ይህ አስተያየት ሰጪ በጎንደር ዩንቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሲፈተኑ የነበሩ ተማሪዎች ፈተናውን አቋርጠው እንደወጡም ጠቅሷል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በሸሜን ሽዋ ዞን የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ ሲሆን በከተማዋ ዙሪያ እና አካባቢው ከትናንት በስቲያ የተጀመረው ውጊያ ዛሬም እንደቀጠለ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በተባባራሪ ጥይት ተመተው ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች ቁጥር በየቀኑ እያጋጠመ ነው የሚለው ይህ አስተያየት ሰጪ እስካሁን ከ10 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
የዋግ ህምራ ዞን ዋና መቀመጫ በሆነችው ሰቆጣ እና አካባቢው በአንጻራዊነት ሰላም እንደሆነ ስሙ እንዳይጠቀስ ከፈለገ የከተማዋ ነዋሪ ሰምተናል፡፡
ከሰሞኑ በሕወሃት ታጣቂዎች በዛታ እና አብርገሌ ወርቅዲብኑ በኩል ከተሞከረው ትንኮሳ በስተቀር አካባቢው ሰላም መሆኑንም ይሄው ነዋሪ ነግሮናል፡፡
የመንግስት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም መደበኛ አገልግሎታቸውን በመስጠት ላይ እንደሆኑም ነዋሪው ተናግሯል፡፡
የሕወሃት ታጣቂዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ እና በትናንትናው ዕለት ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱ ስፍራዎች ጥቃት ለመክፈት ሞክረው በአካባቢው ባለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በሚኒሻዎች መመከት ተችሏልም ተብሏል፡፡
ይሁንና ወደ ደብረታቦር፣ ወልደያ እና ላሊበላ የሚያስኬዱ መንገዶች ከሰሞኑ መዘጋታቸው በነዋሪዎች ላይ ስጋት ደቅነዋል ያለን ሲሆን ወደ ወልደያ የሚያስኬደው መንገድ አሁን ላይ በተወሰነ መንገድ ክፍት መሆኑንም አክሏል፡፡
በዋግ እና አካባቢው ኢንተርኔት ከተዘጋ ሶስት ቀን እንደሆነ እና የመንገዶች መዘጋት ህዝቡ ዳግም ወደ ምግብ እና ሸቀጣ ሸቀጦች እጥረት እንዳንገባ ሲል ስጋት ገብቶታል ተብሏል፡፡
አል ዐይን አማርኛ የህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረዋል የሚለውን ማረጋገጥ አልቻለም።
በተመሳሳይ በጎጃም ዞኖችም ግጭቶች መስተዋላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አማራ ክልል ጎጃም አካባቢ ደግሞ የተለያዩ ከተሞች ለቀናት ተዘግተዋል። ነዋሪዎች መውጫና መግቢያ መንገዶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ባንኮች መዘጋታቸውን ገልጸው፤ እንቅስቃሴም ለቀናት መገደቡን ተናግረዋል።
ነዋሪዎች እንደተናገሩት ታጣቂዎች ፖሊስ ጣቢያዎችን ጨምሮ አንዳንድ የመንግስት ተቋማትን ይዘዋል።
አይንአዲስ የተባሉ በንግድ ስራ የተሰማሩ የደብረ ማርቆስ ነዋሪ ከረቡዕ ሀምሌ 26 ጀምሮ መደበኛ እንቅስቃሴ ተቋርጦ፤ ከመንግስት ጋር ግጭት መከሰቱን ተናግረዋል።
ከተማዋ "በፋኖ" ታጣቂዎችና በህዝቡ "ቁጥጥር ስር" መሆኗንም ገልጸዋል።
ትናንት ሀሙስ በከተማዋ በሚገኘው የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ለመግባት የሞከሩ ሰዎች፤ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው አንድ ሰው መገደሉንና ብዙዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
"በታጣቂዎችና በህዝቡ መሀል ልዩነት የለም" ያሉት አይንአዲስ፤ የፖሊስ ማሰልጠኛው ለመያዝ የሞከረው ነዋሪው ነው ብለዋል።
አጠቃላይ ሰሞነኛ ሁነቱንም "ህዝባዊ አመጻ" ብለውታል።
ህዝቡ መንገድ እየተዘጋበትና እየታገተ ሲበደል በመክረሙ ምሬት ላይ ነው ያሉት ነዋሪዋ፤ ልዩ ኃይል ከመፍረስ ጋር ተያይዞ ግን ውጥረቱ መካረሩን ተናግረዋል።
የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጥቃት አድራሾች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ክንዳቸውን ሰላማዊ ህዝብ ላይ አሳርፈዋል በማለትም ወቅሰዋልም።ግጭቱ በኃይል እንደማይረግብ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አስተያየት ሰጪ ደግሞ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ ሲሆን ከተማዋ እና የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ ከመንግስት የጸጥታ መዋቅር ቁጥጥር ውጪ እንደሚገኙ ተናግሯል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ አገልግሎት ማቋረጡንና ለማረፍ ተቃርቦ የነበረ አውሮፕላን መመለሱንም ነው የገለጸው።
የከተማዋ አሁናዊ ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑንና በህብረተሰቡ ላይ የተፈጠረ ችግር እንደሌለም ይናገራል።
በዞኑ የመቄት ወረዳ እና የጋሸና ከተማ አስተዳደር ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ በ”ፋኖ” ስለመያዛቸው አል ዐይን ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጧል።
በጋዞ ወረዳ እስታይሽ ከተማ እና ከወልዲያ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ሳንቃ ከተማ አካባቢ ከባድ ውጊያ ሲደረግ መሰንበቱን ነው ነዋሪዎች የነገሩን።
“ውጊያው አሁን ቆሟል፤ ተዘግቶ የነበረው የወልዲያ ጋሸና መንገድ ዛሬ ተከፍቷል” የሚሉት የጋሸና ከተማ ነዋሪ አቶ ሰማኝ፥ የጸጥታ ስጋቱ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን አልሸሸጉም።
ካሳለፍነው ማክሰኞ ረፋድ ጀምሮም የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡንና የተከፈተው መንገድ ዳግም ሊዘጋ ይችላል የሚል ስጋታቸውንም አክለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን መናገሻ ወልዲያን ጨምሮ በተለያዩ የዞኑ ከተሞች ላይ በጸጥታ ሁኔታው ምክንያት የመንግስት ተቋማት በሚገባ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በክልሉ ያለውን ሁኔታ በመደበኛ የጸጥታ ማስከበር መቆጣጠር እንደማይቻል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ጣልቃ እንዲገባ የተጠየቀው የፌደራል በዛሬው መንግስትም በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ወስኗል፡፡