የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በአማራ ክልል ያለው ግጭት በውይይት እንዲፈታ ጠየቀ
ም/ቤቱ ጦርነት ቁሳዊ እና ሰብአዊ ውድመት ከማስከተል ውጭ "የችግር መፍትሄ እንደማይሆን ከቅርብ ጊዜው ተሞክሯችን መማር አለመቻላችን አሳዛኝ ነው" ሲል ገልጿል።
የፌደራል መንግስት በክልሉ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትናንትናው እለት አውጇል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት በወይይት እንዲፈታ ጥሪውን አስተላልፏል።
ምክርቤቱ እንደገለጸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት(የግጭቱ ተሳታፊዎች) አክሳሪ ከሆነው የጦርነት መንገድ ወጥተው በአስቸኳይ ወደ ውይይት እንዲመጡ ጠይቋል።
በአማራ ክልል ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ችግር እየተከታተለው መሆኑን የገለጸው ም/ቤቱ የሁለት አመቱ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት "ካደረሰብን ዘርፈ ብዙ ችግር በቅጡ ባለገገምንበት በዚህ ወቅት፣ ወደ ሌላ መጠነ ሰፊ የእርስበእርስ ግጭት መግባት በህዝባችን" ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ችግር ይፈጥራል ብሏል።
ም/ቤቱ ጦርነት ቁሳዊ እና ሰብአዊ ውድመት ከማስከተል ውጭ "የችግር መፍትሄ እንደማይሆን ከቅርብ ጊዜው ተሞክሯችን መማር አለመቻላችን አሳዛኝ ነው" ሲል ገልጿል።
በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር የተፈጠረው ባለፈው ሚያዝያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ እና መልሰው እንዲደራጁ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነበር።
በክልሉ በርካታ ከተሞች "የአማራ ልዩ ኃይል መፍረስ የለበትም" የሚሉ ተቃውሞዎች በሰፊው መደረጋቸውም ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት ይህን ውሳኔ በማይቀበሉ አካላት ላይ "የህግ ማስከበር እርምጃ" መውሰድ መጀመሩን አስታውቆ ነበር፤ እርምጃው አሁንም እንደቀጠለ ነው።
መንግስት ወደ እርምጃ መግባቱን ተከትሎ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች ግጭት መከሰቱን እና በዚህም በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች በተለያየ ጊዜ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
አሁን ግጭቱ ተባብሷል።
የአማራ ክልል፣ የፌደራል መንግስት የክልሉ የጸጥታ ችግር ከአቅሙ በላይ መሆኑን እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ጠይቋል።
ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በክልሉ ለስድስት ወራት ተፈጼሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትናንትናው እለት አውጇል።