በኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ ገለጸ
በኢትዮጵያ በዚህ አመት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብአቂ እርዳታ እንደሚፈልጉ ኮሚሽኑ አስታወቀ
በኢትዮጵያ በዚህ አመት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብአቂ እርዳታ እንደሚፈልጉ ኮሚሽኑ አስታወቀ
በኢትዮጵያ በዘንድሮው አመት 15.1 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ዜጎቹ ድጋፍ የሚፈልጉት የኮሮና ቫይረስ ፣ግጭቶች፣ጎርፍ፣ድርቅና የአንበጣ ወረርሽኝ ባስከተሉት ተጽዕኖ ለችግር በመዳረጋቸው መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
በክረምቱ በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መጎዳታቸውን አቶ ደበበ ገልጸዋል፡፡ በጎርፍ ሳቢያ በአጠቃላይ በ33 ዞኖችና በ110 ወረዳዎች ከ342 ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በጎርፍ ሳቢ ከተፈናቀሉት ከ46 ሺ በላይ ዜጎች 96 በመቶው አሁን ላይ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆናቸውንም ነው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በጥቅሉ ድጋፍ ለሚሹት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአጠቃላይ ድጋፍ የሚስፈልገው የገንዘብ መጠን 1 ነጥብ 44 ቢሊዮን ዶላር ወይንም በወቅታዊው የምንዛሬ ዋጋ 53 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አቶ ደበበ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ለምግብ ከሚያስፈልገው ገንዘብ መካከል እስካሁን 67 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ የተገኘ ሲሆን ምግብ ነክ ላልሆኑ ማለትም ለጤና፣ ለንጽሕና፣ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለውኃና ለንጽህናና ለሌሎችም ከሚያስፈልገው ውስጥ 32 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት 187 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ያነሱት አቶ ደበበ ከለጋሽ ድርጅቶች ደግሞ 478 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አንስተዋል፡፡ በዘርፉ የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት እንደገለጹት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ እያጋጠመ ሲሆን የዘንድሮ ግን ከ30 ዓመታት በኋላ ከፍተኛ የጎርፍ ክስተት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ የምላሽ መስጠትና መልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ደበበ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚመለከታቸው ተቋማትና ግለሰቦች የሚችሉትን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡