በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ ተከትሎ አራት ወረዳዎች በኮማንድ ፖስት ስር ገብተዋል
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ ተከትሎ አራት ወረዳዎች በኮማንድ ፖስት ስር ገብተዋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው “አሰቃቂ ጥቃት” አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
በክልሉ በሀምሌ 20 እና ጳጉሜ 1 የክልሉ መንግስት ጸረ-ለውጥ ኃይሎች ባላቸው ታጣቂዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን ግድያውን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
ነገርግን ግድያው ሊቆም አልቻለም፤ በድጋሚ መስከረም 15 ተጨማሪ 15 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡
ኢስመኮ "የዜጎችን ደሕንነት ማረጋገጥ እና ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል!" ያለ ሲሆን “በድጋሚ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉ በእጅጉ አሳሳቢነቱን እንደጨመረ” ነው ብሏል፡፡
“መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ በመተከል ዞን፣ ዳንጉር ወረዳ፣ ማንቡክ ከተማ በንገዝ ወንዝ አካባቢ በሚገኝ መንደር በታጠቁ ሰዎች በተከፈተ ተኩስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን” ኮሚሽኑ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ኢሰመኮ በጥቃቱ 15 ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት አልፏል ብላል፡፡
መከላከያ ሰራዊት የተጎዱ ሰዎችን በመፈለግ ላይ መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ገልጿል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በክልሉ “ጸጥታን ማስፈን፣ የሕግ በላይነትን ማረጋገጥና በሲቪል ሕዝብ ላይ አሰቃቂ ጥቃት እያደረሱ ያሉትን አጥፊዎች”በአስቸኳይ ለፍትህ መቅረብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ከመስከረም 14 ጀምሮ በመተከል ዞን የሚገኙ የጸጥታ ችግር ተስተውሎባቸዋል የተባሉት አራት ወረዳዎችን በኮማንድ ፖስት ለማስተዳደር የፌደራል መንግስት ወስኗል፡፡