36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምራል
ኮሞሮስ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርነትን ተረከበች።
36ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ፣ የናይጀሪያ፣ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች ተገኝተዋል።
ላለፉት 12 ወራት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የነበሩት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የህብረቱ የሊቀመንበርነት ስልጣንን ለወቅቱ ተረኛ ለሆነችው ኮሞሮስ ፕሬዝደንት አዛሊ አሱማኒ አስረክበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት ስልጣን በየዓመቱ የህብረቱ አባል ሀገራት እየተፈራረቁ የሚመሩት ሲሆን የ2023 ተረኛ ሀገር ደቡብ አፍሪካዊቷ ኮሞሮስ ሆናለች።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሀማት በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ አሁንም የደህንነት ፣ የገንዘብ እና ዝቅተኛ የእርስ በርስ ንግድ እንቅስቃሴ ችግር እንዳለባት ተናግረዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት የህብረቱን የእርስ በርስ ንግድ፣ መሰረተ ልማት፣ ድጅታላይዜሽን እና የሰዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ እድሎችን የሚያሰፋ በመሆኑ አፍሪካዊያን የስምምነቱን መተግበር እንዲደግፉ አሳስበዋል።
ህብረቱ መፈንቅለ መንግሥት ያደረጉ አባል ሀገራትን ከአባልነት ቢያግድም ማዕቀቡ የታሰበውን ያህል ለውጥ አለማምጣቱንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ስምምነት የፈጸሙትን እና ሌሎች እገዛዎች ላደረጉ ሀገራት እና ተቋማትም ሙሳ ፋኪ ምስጋና አቅርበዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በአፍሪካ የምግብ እና ሌሎች ምርቶች ላይ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት አድርጋል ያሉት ኮሚሽነሩ አፍሪካዊያን ሀገራት ህብረቱ እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን የፋይናንስ እና ሌሎች ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።