የአፍሪካን ገናናነት የሚያሳዩ 5 ድንቅ ሙዚየሞች
አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር በአፍሪካ ሊጎበኙ ይገባቸዋል ብሎ ከዘረዘራቸው ሙዚየሞች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ቀዳሚ ነው
ሙዚየሞቹ አፍሪካ በሰለጠነው አለም የተሰጣትን ስያሜ የሚያስለውጡ ናቸው ተብሏል
አፍሪካ ከጥንታዊ የአክሱም፣ ኑቢያ እና ግብጽ ስልጣኔዎች አንስቶ ረጅም የታሪክ ባለቤት አህጉር ናት።
የሰው ልጅ ፍጥረት ተደርጋ የምትነሳው አህጉር፥ በእምነት፣ ባህልና ቋንቋም የዳበረ ታሪክ እንዳላት ተመራማሪዎች ያነሳሉ።
ይህ የስልጣኔ እና ታሪክ ዘውዷም በገነባቻቸው ሙዚየሞች በጉልህ ይንጸባረቃል።
አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ይዞት በወጣው ዘገባም፥ ስለአፍሪካ የሰለጠነው አለም ያለውን ምልከት የሚቀይሩ ናቸው ያላቸውን አምስት ሙዚየሞች ይፋ አድርጓል።
1. የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም
የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን እድሜ ያላት ሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪት አካል መገኛ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፥ በብሄራዊ ሙዚየሟ የሚሊየኖች ታሪክ ይዛለች። ለሳይንሳዊ ምርምሮች መሰረት ከሆኑት ባሻገር ህብር ያላቸው ኢትዮጵያውያንን የአለባበስ፣ አመጋገብና ሌሎች ባህሎች በዚሁ ሙዚየሟ ስታሳይ ትውላለች። የኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ እና ቅርሶችን መመልከት አፍሪካንም ያሳያልና ይጎብኙት ይላል አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር።
2. የግብጽ ሙዚየም
በአባይ ላይ የተመሰረተው የግብጽ የስልጣኔ አብዮት ሺህ አመታትን ቢያስቆጥርም ዘመኑን የሚያወሱ ቅርሶች በካይሮ በሚገኘው የግብጽ ሙዚየም ይገኛሉ።
የፈርኦኖቹን መገልገያ ቁሳቁሶች በስፋት ለእይታ የሚያቀርበው ሙዚየም በአፍሪካ ትልቁ የአርኪዮሎጂ ሙዚየም መሆኑ ይነገራል።
የጥንት ግብጻውያን የድንጋይ ላይ ጽሁፎች፣ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦች እና የአስከሬን የማድረቅ ጥበባቸውም በየአመቱ በሚሊየኖች ይጎበኛሉ።
3. የአፓርታይድ ሙዚየም - ደቡብ አፍሪካ
ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ከ1948 እስከ 1994 ሲደርስባቸው የነበረውን ጭቆና የሚያሳየው የአፓርታይድ ሙዚየም በአፍሪካ ሊጎበኙ ከሚገባቸው ሙዚየሞች ተካቷል። በጆሃንስበርግ በሚገኘው ሙዚየም ደቡብ አፍሪካውያን ለነጻነት እና እኩልነት የከፈሉት መስዋዕትነት ከመነሻው እስከመድረሻው ይታያል። ግፍ እና ጭቆና የወለደውን ትግል የሚያሳዩ ታሪካዊ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችም ለእይታ ይቀርቡበታል።
4. የጥቁሮች ስልጣኔ ሙዚየም - ሴኔጋል
የአፍሪካውያንን ታሪክ እና ባህል ለማጥናት የሚፈልግ ሰው ሳይጎበኘው እንዳይቀር የተባለው ሌላኛው ሙዚየም ደግሞ በሴኔጋል ዳካር የሚገኘው የጥቁሮች ስልጣኔ ሙዚየም ነው። አፍሪካ ለሌላው አለም ያስተዋወቀቻቸው ባህላዊ እሴቶች፣ የስነጽሁፍ እና ቅርጻ ቅርጽ ጥበብ በዚህ ሙዚየም ግዘፍ ነስቶ ይታያል። የአፍሪካ ቅርሶች በአለም አቀፍ ደረጃ የፈጠሩትን ተጽዕኖ ለማየት ዳከር መገኘት ይገባል ይላል የአፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ።
5. የናይሮቢ ብሄራዊ ሙዚየም
የምስራቅ አፍሪካን ድንቅ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ቅርሶች በአንድ ጣሪያ ስር ለመመልከት ካሻችሁ በኬንያ የሚገኘውን የናይሮቢ ብሄራዊ ሙዚየም እንዲጎበኙት ይመከራል። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ድንቅ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ያሏት ኬንያ፥ ለተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለጎብኝዎች ወደጥንታዊ ታላቅነት የሚመልሱ የሰው ልጆች የእጅ ውጤቶችን ታስመለክታለች።
አፍሪካ በድህነት “ሶስተኛው አለም” በሚለው የሰለጠኑት ሀገራት ምደባ ውስጥ ብትገባም ሙዚየሞቿ የቀደመ ገናናነቷን ያሳያሉ።
አፍሪካውያን እነዚህን ሙዚየሞች ሲጎበኙ የሚጋባው ስሜትም የቀደሙት አባቶች የመቻል መንፈስ እንደሆነ የአፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ ያመለክያል።
እርሶስ ከአምስቱ የአፍሪካ ድንቅ ሙዚየሞች ስንቱን ጎብኝተዋል?