ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት አፍሪካዊያን ላሳዩት ድጋፍ አመሰገነች
የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ያቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን እንዲፈርስም ኢትዮጵያ7 ጠይቃለች
የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀምሯል
ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት አፍሪካዊያን ላሳዩት ድጋፍ አመሰገነች።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት አባል የሆኑበት የህብረቱ ስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
- ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በመንግስትና በህወሓት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ምን አሉʔ
- ውይይቱ “የሰላም ስምምነቱ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል” የሚል መንፈስ ፈጥሯል - አምባሳደር ወንድሙ
በዚህ ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን አፍሪካዊያን ለኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ጦርነቱን ተከትሎም ያለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ጫናዎች ሲደረጉ ነበር ያሉት አቶ ደመቀ አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ላሳዩት ድጋፍ ምስጋና ይገባችኋልም ብለዋል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተፈረመው የሰላም ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ እንደሚተገበርም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
አቶ ደመቀ አክለውም የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ምርመራ የሚያደርግ የሰብዓዊ መብት ምርመራ የባለሙያዎች ቡድን መቋቋሙ እና የስራ ጊዜው ለአንድ ዓመት መራዘሙን ተችተዋል።
በመሆኑም አፍሪካዊያን ሀገራት እና ተቋማት ይህ የባለሙያዎች ቡድን እንዲፈርስ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥያቄ እንዲደግፉ ሲሉ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ይህን የባለሙያዎች ቡድን እንዲፈርስ ከመጠየቅ ባለፈ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንዲሰራ እንደማትፈቅም ጠቅሰዋል።
ይህ የባለሙያዎች ቡድን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተፈረመው የሰላም ስምምነቱን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ ከዚህ በፊት በተመድ ሰብዓዊ መብት እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እና የመፍትሔ ሀሳቦች እንዳይተገበሩ የሚያደርግ እንደሆነም አቶ ደመቀ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አክለዋል።
የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ዛሬ እና ነገ የሚካሄድ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ለሚካሄደው 36ኛው የመሪዎች ስብሰባ የውይይት አጀንዳዎችን እና የውሳኔ ሀሳቦችን ማስቀመጥ የውይይቱ ዋነኛ አላማ ነው።