የኮንጎው አማጺ ቡድን ኤም-23 ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
ኮንጎን ጨምሮ አራት ሀገራት የምስራቅ ኮንጎን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከስምምነት ደርሰዋል
የኮንጎ መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጀው ኤም-23 ጋር ድርድር ማድረግ የማይታሰብ ነው ብሏል
የኮንጎው አማጺ ቡድን ኤም-23 ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑ ገለጸ፡፡
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማፂ ቡድን ኤም- 23 ይህን ያለው በትናንትናው እለት የኮንጎ ፕሬዝዳንት እና ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች የሚሊሻዎችን ጥቃት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ መሆኑ ነው፡፡
የኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና አንጎላ መሪዎች በዚህ ሳምንት በሉዋንዳ ተገናኝተው በሺዎች የሚቆጠሩ ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት የሆነውን የምስራቅ ኮንጎ ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከስምምነት መድረሳቸው ሮይተረስ ዘግቧል፡፡
መሪዎቹ ከአርብ ጀምሮ የተኩስ አቁምን እናስፈጽማለን የሚል ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ኤም -23 ከተቆጣጠረው ስፍራ ለቆ ካልወጣ በአከባቢው ወታደሮች ጣልቃ ይገባሉ ብለዋል።
የስምምነቱ አካል ባይሆንም የስምምነቱን ይዘት በማህበራዊ ሚዲያ ማወቁ የገለጸው ኤም-23 በቃል አቀባዩ ላውረንስ ካንዩካ በኩል በሰጠው መገለጫ "የቀጠናው አመራሮች አሁን የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ላደረጉት ጥረት እናመሰግናለን" ብሏል።
የኤም-23 መሪ በርትራንድ ቢሲምዋ በበኩላቸው "የእነዚህን ሁሉ ጦርነቶችና እዚህ እየፈጠሩ ያሉትን የግጭት መንስኤዎችን ለመፍታት ከመንግስት ጋር ቀጥተኛ ድርድር እንፈልጋለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ የኮንጎ መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጀው ኤም -23 ጋር ድርድር እንደማይደረግ አስታውቋል።
ሃሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ “ይህ አይሆንም፣ በመንግስት እና በሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ስም ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ኤም -23 ቀደም ሲል በሚያዝያ ወር የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ማወጁንና ጥቃቶችን እየጀመረ ያለው የኮንጎ ጦር ነው የሚል ክስ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።
ሆኖም ጦርነቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ ሲሆን ኤም -23 በኮንጎ ምስራቅ የሚገኙ በርካታ ከተሞችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ኤም-23 እንደፈረንጆቹ በ2012 የተመሰረተ አማጺ ቡድን ሲሆን በሩዋንዳ እንደሚደገፍ ኮንጎም ሆነ የተመድ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይደመጣል፡፡
የአሁኑ ስምምነት አካል የሆነችው የፖል-ካጋሜዋ ሩዋንዳ ግን ክሱ መሰረተ ቢስ እንደሆነ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡