ዲሞክራቲክ ኮንጎ የሩዋንዳ አምባሳደር ኬንሻሳን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
የሩዋንዳ አምባሳደር የተባረሩት ሀገራቸው ኤም23 የተሰኘውን አማጺ ቡድን ትረዳለች በሚል ነው
ዲሞክራቲክ ኮንጎ የሩዋንዳ አየር መንገድ ወደ ሀገሯ እንዳይበር ማገዷ ይታወሳል
ዲሞክራቲክ ኮንጎ የሩዋንዳ አምባሳደር ኬንሻሳን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች፡፡
ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ኤም23 የተሰኘው አማጺ ቡድን የሚንቀሳቀስ ሲሆን ይህ አማጺ ቡድን ከሩዋንዳ ወታደራዊ እና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያገኝ ኬንሻሳ እምነት አላት፡፡
ይሄንን ተከትሎም ዲሞክራቲክ ኮንጎ በይፋ ሩዋንዳ ኤም23 የተሰኘውን አማጺ ቡድን መደገፍ እንድታቆም የጠየቀች ቢሆንም ሩዋንዳ በበኩሏ ክሱን ውድቅ አድርጋለች፡፡
ይህ አማጺ ቡድን ከሰሙኖ ሁለት ከተሞች መቆጣጠሩን ተከትሎ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በሀገሯ ያሉ የሩዋንዳ አምባሳደር ለማባረር መወሰኑ ተገልጿል፡፡
የመንግስት ቃል አቀባዩ ፓትሪክ ሙያያ ለሮይተርስ እንዳሉት መንግስት ከሰሞኑ ባደረገው የደህንነት ስብሰባ ሩዋንዳ አሁንም ለኤም23 አማጺ ቡድን ድጋፍ ማድረጓን እንዳላቆመች ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት በኬንሻሳ ያሉት የሩዋንዳ አምባሳደር በ48 ሰዓት ውስጥ ዲሞክራቲክ ኮንጎን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
የኤም23 አማጺ ቡድን አዲስ ጥቃት በአካባቢው ያለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር ቁጥሩን እንዲያሳድግ ማድረጉንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ በዚህ አማጺ ቡድን ምክንያት ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በመበላሸት ላይ ሲሆን የሩዋንዳ አየር መንገድ ወደ ኬንሻሳ እንዳይበር ከስድስተ ወር በፊት እገዳ ተጥሎበታል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ በአንጎላ መዲና ሉዋንዳ ተገናኝተው የመከሩ ቢሆንም የመሪዎቹ ውይይት ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ሀገራቸው ኤም23 የተሰኘውን አማጺ ቡድን ትደግፋለች በሚል ለሚቀርብባቸው ጥያቄ የዚህ አማጺ ቡድን ጉዳይ እኛን አይመለከትም የዲሞክራቲክ ኮንጎ የውስጥ ጉዳይ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡