የኤም23 አማጽያን በዲ.አር ኮንጎ የሚኖሩ ቱትሲዎችን ለመጠበቅ በሚል ነፍጥ አንግበው እንደሚንቀሳቀሱ ይነገራል
አሜሪካ፣ ሩዋንዳ የኮንጎ አማጽያንን ትረዳለች መባሉ እጅግ እንዳሳሰባት ገለጸች፡፡
ሩዋንዳ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሱ የኤም23 አማጽያንን ታስታጥቃለች መባሉ አሜሪካን እጅግ ማሳሰቡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒዮ ብሊንከን ተናግረዋል፡፡
ብሊንከን በሰሞነኛው የአፍሪካ ጉብኝታቸው ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጎራ ብለው ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሲሺኬዲ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር በሃገሪቱ የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በዋናነት በምስራቃዊ የሃገሪቱ አካባቢ ስላጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ አማጽያን ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በውይይቱም ሩዋንዳ አማጽያኑን እንደምትረዳ ተገልጾላቸው፡፡
አሜሪካ ሁኔታው እጅጉን እንደሚያሳስባት የተናገሩት ብሊንከንም አማጽያኑን መደገፍና መተባበር እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኪንሻሳ ቆይታቸው ሲጠናቀቅ ወደ ሩዋንዳ ነው የሚያቀኑት፡፡ በኪጋሊ በሚኖራቸው ቆይታ ስለ ጉዳዩ ከሩዋንዳ ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩም ገልጸዋል፡፡
ኤም23 (May23) የ1994ቱ የሩዋንዳ ጭፍጨፋ ቅሪት መሆኑ ይነገራል፡፡ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ ቱትሲዎችን ከሁቱዎች እጠብቃለሁ በሚልም ነው ከፈረንጆቹ 2012 ወዲህ ነፍጥ አንግቦ በምስራቃዊ የሃገሪቱ አካባቢዎች መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ ይህም በፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በሚመራው የሩዋንዳ መንግስት ይደገፋል ለመባሉ ምክንያት ሆኗል፤ ምንም እንኳን ሩዋንዳም ሆነች አማጽያኑ ስለ ድጋፉ ቢያስተባብሉም፡፡
በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በፈጸማቸው ተከታታይ ጥቃቶች በርካቶችን መግደሉና ማፈናቀሉ የሚነገርለት አማጺ ቡድኑ ባሳለፍነው ሃምሌ ወር ብቻ ባደረጋቸው ተከታታይ ዘመቻዎች ሰፊ ቦታዎችን መቆጣጠሩንና ይዞታዎቹን ማጠናከሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል እንደ ሮይተርስ ዘገባ፡፡