ዝርፊያውን የፈጸሙት በ 100ዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ናቸው ተብሏል
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ቢሮ ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ገለጸ።
በሀገሪቱ የሚገኘው ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በቢሮዎች ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረበት ይፋ አድርጓል። ቢሮው ዝርፊያ የተፈጸመበት ተቃውሞ ባነሱ የኮንጎ ዜጎች መሆኑም ተገልጿል።
ጥቃቱን የፈጸሙት፤ በኮንጎ ያለው የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ዜጎችን መጠበቅ ስላልቻለ ከሀገር ለቆ ይዉጣ የሚል ጥያቄ ያነሱ ዜጎች ናቸው ተብሏል።
ተልዕኮው ሀገር ለቆ እንዲወጡ ፍላጎት ያላቸው ተቃዋሚዎቹ፤ ተቋሙን ከማጥቃትም ባለፈ ዘረፋ መፈጸማቸውም ተገልጿል።
በኮንጎ የተመድ ሰላም አስከባሪ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ጥቃት ያደረሱ የኮንጎ ተቃዋሚዎች በቀጥታ ወደ ቢሮ በመግባት ዘረፋ መፈጸማቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ገልጿል።
በስፍራው የነበሩ የተመድ ሰራተኞች በዚህ ድርጊት መደንገጣቸውንም ነው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀው።
በኮንጎ ተቃውሞ ያነሱት እነዚህ ዜጎች ወደ ተመድ ቢሮ የሚወስደውን መንገድ በአለት በመዝጋትና እሳት በማቀጣጠል ዝርፊያውን ፈጽመዋል ተብሏል።
እስካሁን በተጠናቀረ መረጃ መሰረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሰላም አስከባሪ ቢሮ መጋዘኖች በመግባት ዝርፊያ ፈጽመዋል ተብሏል።
ዝርፊያው የተፈጸመው በምስራቅ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግዛት በምትገኘው ጎማ ከተማ መሆኑም ተገልጿል። የጎማ ከተማ የሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ስትሆን ከኪቩ ሃይቅ በስተሰሜን አቅጣጫ ትገኛለች።