ሚኒስትሩን ለመክሰስ የሪፐብሊካን ምክር ቤት አባላት የሕግ አንቀጾችን እየፈለጉ ነው ተብሏል
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የገቡትን የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ባለመቻላቸው እንዲከሰሱ ተጠይቋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዲከሰሱ የጠየቁት የሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ምክር ቤት የገቡ አባላት መሆናቸውን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡ አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኃላፊነት ሲመጡ የገቡትን ቃል ማሳካት እንዳልቻሉ የገለጹት አባላቱ በዚህም ምክንያት መከሰስ አለባቸው በሚል የሀገሪቱን ሕጎች እየጠቀሱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ብዙ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በብሊንከን ላይ ጥያቄ ቢኖራቸውም የሚሪላንድ ተወካዩ አንዲ ሃሪስ እና የደቡብ ካሮላይና ተወካዩ ራልፍ ኖርማን ግን የሕግ አንቀጾችን ሳይቀር እያጣቀሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒትሩ መከሰስ እንዳለባቸው መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
የአፍጋኒስታን ጉዳይ እንዲሻሻል መሰራት ቢገባውም ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ ከፍተኛ መቅሰፍት መድረሱን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡ የአፍጋኒስታንን ጉዳይ ማስተካከል በፕሬዝዳንት ባይደን ትከሻ ላይ የወደቀ ቢሆንም በዋናነት ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የማማከር ኃላፊነት ነበረባቸው ተብሏል፡፡
ከትናንት በስቲያ በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል ሃሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አወሮፕላን ማረፊያ ውጭ ላይ በተከሰተው ፍንዳታ 13 የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸው እና ምስቅልቅል የበዛበት ወታደሮችን የማስወጣት ተግባርም አንቶኒ ብሊንከንን ሊያስጠይቅ እንደሚችል የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ፤ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት በሚጠበቅባቸው ልክ አለማማከራቸው እና አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያላትን ብሐየራዊ ጥቅም በተገቢ ሁኔታ ማሳወቅ አለመቻላቸው ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ነው የተገለጸው፡፡
የምክር ቤት አባላት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዲከሰሱ ቢጠይቁም ፤ ሌሎች ደግሞ በካቡል ሃሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አወሮፕላን ማረፊያ ውጭ ላይ በተከሰተው ፍንዳታ 13 የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸው በተለያየ ደረጃ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ሕገ መንግስት መሰረት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት በተመለከተ ለኮንግረንሱ እና ለሕዝቡ ማሳወቅ እንዳለባቸው ቢደነግግም አንቶኒ ብሊንከን ግን ይህንን አለማድረጋቸውን የምክር ቤቱ አባላት ጠቅሰዋል ተብሏል፡፡ በታሊባንን ቁጥጥር ስር ባለ ሀገር የአሜሪካን ዜጎች ለአደጋ አጋልጦ በመውጣት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ተጠያቂ እንዲሆኑ ክስ ይቅርብባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፎክስ ኒውስ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት የሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ምክር ቤት የገቡ አባሎች አንቶኒ ብሊንከን እንዲከሰሱ ፍላጎት አላቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ሆነ ከራሳቸው ከአንቶኒ ብሊንከን የተሰማ አስተያየት አለመኖሩንም ፎክስ ኒውስ ጽፏል፡፡