የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣት በታሪካችን ትልቁ ውርደት ነው” አሉ
ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣት ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል
“ውሳኔው የፕሬዝዳንት ባይደን እጅግ በጣም አስገራሚ የአቅም ማነስ ማሳያ ነው”ም ብለዋል ትራምፕ
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣት በታሪካችን ትልቁ ውርደት ነው” ሲሉ ተናገሩ፡፡
አፍጋኒስታንን ለታሊባን ያስረከቧት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ናቸው ሲሉ የሚወቅሱት ትራምፕ በአሁኑ ወቅት “የታሊባን እንቅስቃሴ በዋጋ ሊተመን የማይችል የተራቀቁ መሣሪያዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል” ሲሉም ነው በአላባማ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር የገለጹት፡፡
“ያልተሳካው የባይደን ከአፍጋኒስታን የመውጣት ሂደት የፕሬዝዳንቱ እጅግ በጣም አስገራሚ የአቅም ማነስ ማሳያ ነው፤ ምናልባትም በአሜሪካ ታሪክ ያልሆነ የማይሆንም ነው” ሲሉም ተናግረዋል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፡፡
በአፍጋኒስታን የነበሩ የአሜሪካ ዜጎችንና ሰራተኞችን አደጋ ላይ ለጣለው የመውጣት ሂደት እንዲሁም ለተፈጠረው ክፍተት ፕሬዝዳንት ባይደን ኃላፊነት የሚወስዱ ይሆናል ያሉት ትራምፕ ሂደቱን “መውጣት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እጅ መስጠት ነው” ብለውታል፡፡
በውሳኔያቸው እንደማይጸጸቱ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ባይደን በበኩላቸው አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ወታደሮቿን ማስወጣቷ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን እንዲሁም በአፍጋኒስታን የተፈጠረው ክፍተት እየተንከባለለ የመጣና በትራምፕ ዘመንም ቢሆን መቋጫ ሳያገኝ የቆየ ጉዳይ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
የአሜሪካ ጦር ሽብርተኞችን ለመዋጋት እንጂ ሃገር ለመገንባት አፍጋኒስታን አልቀዘለቀም ሲሉ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡
የአፍጋኒስታን ጦር በመጨረሻዋ ሰአት ለመዋጋት ፈቃደኛ አለመሆኑን በመጠቆም የአፍጋኒስታን መንግስትን ማውገዛቸውም የሚታወስ ነው፡፡