የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዜጎችን ከአፍጋን በማስወጣቱ ሂደት ለነበራት ሚና ዩኤኢን አመሰገኑ
ዩኤኢ እስካሁን 8ሺ 500 የውጭ ዜጎች ከአፍጋኒስታን እንዲወጡ ማገዟም ነው የተነገረው
ዩኤኢ አሜሪካውያን ዲፕሎማቶችና ሌሎችም ከአፍጋኒስታን እንዲወጡ ለማገዝ የሚያስችል ድጋፍን አድርጋለች
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዜጎችን ከአፍጋን በማስወጣቱ ሂደት ለነበራት ሚና ዩኤኢን አመሰገኑ፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን ትናንት ምሽት ከአቡዳቢው ልኡልና ከዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር የስልክ ቆይታን አድርገዋል፡፡
በቆይታቸው ዜጎችን ከአፍጋኒስታን በማስወጣቱ ሂደት የ“ዩኤኢን ሚና እንደሚያደንቁ” የገለጹት ባይደን ዩኤኢን አመስግነዋል፡፡
ዩኤኢ የአሜሪካ፣ የአጋር ሀገራት እና የአፍጋኒስታን ዜጎችን ከአፍጋኒስታን እንዲወጡ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረግች ያለች ሀገር መሆኗ ከአሜሪካው ነጩ ቤተ መንግስት /ዋይት ሃውስ/ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ይህን ተከትሎም ለአቡዳቢው ልኡል ስልክ የደወሉት ባይደን ዩኤኢ ያደረገችውን ድጋፍ በማድነቅ፤ ትብብሩ የሀገራቱን ጠንካራ አጋርነት ያሳየ ተግባር ነው ብለውታል፡፡
መሪዎቹ በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መሰል ትብብርን በሚያደርጉበት ሁኔታ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
ዩኤኢ አስካሁን 8 ሺ 500 የውጭ ዜጎች ከአፍጋኒስታን በአውሮፕላን ማስወጣቷ ይታወቃል፡፡
የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "የውጭ ዜጎችን ከካቡል ወደ ዩኤኢ የማስወጣቱ ሂደት በቀጣዩ ቀናት ተጠናክሮ ይቀጥላል"ብሏል፡፡
የአሜሪካን ጥረት ለመደገፍ 5 ሺ አፍጋናውያንን በጊዜያዊነት ተቀብሎ ለማስተናገድ መስማማቱንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
አፍጋናውያኑ በቀጣዮቹ ቀናት በአሜሪካ አውሮፕላኖች ተጭነው ወደ ዩኤኢ መግባት እንደሚጀምሩም ገልጿል፡፡
የአሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በማስወጣቱ ሂደት 13 ሀገራት ለመተባበር እንዲሁም ሌሎች 12 ሀገራት በመሸጋገሪያነት (ትራንዚት) ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
“አልባንያ ፣ካናዳ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ቺሊ፣ ኮሶቮ፣ ሰሜን ሜቆዴንያ፣ ሜክሲኮ፣ ፖላንድ፣ ኳታር፣ ሩዋንዳ፣ ዩክሬን እና ኡጋንዳ” አስካሁን የአፍጋኒስታን ስደተኞችን ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ የሆኑ ሀገራት መሆናቸውንም ነው ብሊንከን የገለጹት፡፡
ብሊንከን እንደ “ባህሬን፣ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ጀርመን፣ ጣልያን፣ካዛኪስታን፣ክዌት፣ታጃኪስታን፣ቱርክ እና ኡዝበኪስታን የማሳሰሉ ሀገራት በትራንዚትንት ለማገልገል የትብብር ፍላጎት ያላቸው ናቸው”ም ብለዋል፡፡