የ”ቶኪዮ ኦሎምፒክ 2020”መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ዳይሬክተር በዋዜማው ተባረሩ
ዳይሬክተሩ ከ23 አመት በፊት ናዚ ማካሄደው ጭፍጨፋ ላይ በቀለዱት ቀልድ ምክንያት ነው
በነገው ዕለት በሚጀመረው የጃፓን ኦሎምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያ በ4 የውድድር አይነቶች ትሳተፋለች
በነገው ዕለት በጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ለሚከፈተው የኦሎምፕክ ጨዋታ የመክፈቻ ስነ ስርአቱን አንዲያስተባብሩ የተመረጡት ዳይሬክተር ከሀላፊነታቸው ተባረሩ፡፡
ዳይሬክተሩ ከሀላፊነታቸው የተነሱት ከ23 አመት በፊት ናዚ ባካሄደው ጭፈጨፋ ላይ በቀለዱት ቀልድ ምክንያት ነውም ነው ተብሏል፡፡
የኦሎምፒክ ጨዋታ የፕርግራሙን መክፈቻ ስነ ስርአት እንዲያስተባብሩ የተመረጡት ኮሜዲያን ኬንታሮ ኮባያሺ በሚልየን አይሁዶች ያለቁበትን የናዚን ጭፍጨፋ በቀልድ መልክ ከ23 አመት በፊት መናገራቸውን የሚያሳይ አንድ የመድረክ ትእይንት በመውጣቱ ከስራቸው እንደተነሱ የጃፓን የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ ገልፀዋል።
የጃፓኑ ኦሎምፒክ ኃላፊው ሴይኮ ሃሺሞቶ ቪዲዮው “አሳዘኝ የታሪክ እውነቶች” በማለት አጣጥለውታል ፡፡
የዳይሬክተሩ ከስራ መባረር የኦሎምፒክ ጨዋታዎቹን ከመጀመራቸው በፊት ከተከሰቱ መጥፎ ክስተቶች የቅርቡ መሆኑ ነው፡፡ከቀናት በፊት አንድ የሙዚቃ አቀናባሪ ሥነ-ሥርዓቱን ለማከናወን ቀናት በቀሩበት ወቅት ከነበረበት ቡዱን ለቅቆ መውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በጃፓን ኦሎምፒክ ከሚሰተፉት ሀገራት አንዷ ናት፡፡
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ለከፍተኛ የሜዳሊያ ቁጥር ውስጥ ከሚታጩ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ከ1956 እ.አ.አ ጀምሮ ተሳትፎዋ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪነቷም ይታወቃል።
ሀገሪቱ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በሚደረጉ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ እንዲሁም በኦሎምፒክ ሜዳዎች ሰንደቅ ዓላማዎቻቸው ከሚውለበለቡላቸው ሀገራት መካከልም አንዷ ናት።
ኢትዮጵያ ባላት ረጅም የኦሎምፒክ ታሪክ አትሌቲክስ ቅድሚያውን ቢይዝም ዘንድሮ ግን ሀገሪቱ በሌሎች ስፖርቶች እንደምትወዳደር ይጠበቃል።
ከሰሞኑ በጃፓና መዲና ቶኪዮ ከተማ በሚጀመረው 32 ኛው ኦሎምፒክም ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በውኃ ዋና እና በቴኳንዶ እንደምትሳተፍ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አስታውቀዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ወር እና አንድ ወር ተኩል ብቻ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየቱን ያነሱት ዶ/ር አሸብር፤ በዘንድሮው ዓመት ግን ላለፉት ስምንት ወራት ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር ተናግረዋል።
አትሌቶች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ አትሌቶች በአዲስ አበባ ስታዲዮም ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ማሻሻላቸውንና በዓለም ላይ ደግሞ እነ ለተሰንበት ግደይ የሚያኮራ የዓለም ክብረ ወሰን ማሻሻላቸውን ገልጸዋል።
ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማትና ግለሰቦችም ወደ ጃፓን ለሚጓዘው ቡድን የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንቱ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ከ57 ዓመታት ቆይታ በኋላ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዳግም ወደ ቶኪዮ የተመለሱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በወቅቱ በሻምበል አበበ ቢቂላ አሸናፊነት ሰንደቅ ዓላማዋ ተውለብልቦላት እንደነበር የሚታወስ ነው።
እ.ኤ.አ በ 1964 እነ አበበ ቢቂላ ሲወዳደሩባቸው የነበሩ ቦታዎችም ጃፓን ከ57 ዓመት በኋላ ከነገ ጀምሮ የሚካሄዱ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች እንደሚደረጉባቸው ተገልጿል።