“ኮቪድ በቶኪዮ ኦሎምፒክ መጨረሻ ምናልባትም ከ100 ሺ በላይ ሰዎችን ሊገድል ይችላል”- ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ እስካሁን 79 የኮሮና ኬዞች ሪፖርት ተደርገዋል
የኮሮና ወረርሽኝ “ዓለም የከሸፈበት ፈተና ነው” ሲሉ የተናገሩ ዶ/ር ቴድሮስ በክትባቶች ረገድ ያለውን የስርጭት ልዩነት ተችተዋል
ከነገ ወዲያ አርብ የሚጀመረው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ምናልባትም የኮሮና ወረርሽ ዳግም መቀስቀሻ አጋጣሚን ሊፈጥር እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ዛሬ ቶኪዮ ተገኝተው በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በስብሰባው የኮሮና ወረርሽኝ “ዓለም የከሸፈበት ፈተና ነው” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን በመጪው አርብ በቶኪዮ የሚለኮሰው የኦሎምፒክ ችቦ በሚጠፋበት (ውድድሩ በሚጠናቀቅበት) ጊዜ ምናልባትም ከ100 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮና ሊሞቱ ይችላሉ ብለዋል፡፡
እስካሁን በመላው ዓለም 3.5 ቢሊዬን የኮሮና ክትባቶች አገልግሎት ላይ መዋላቸውን በአዎንታ ያነሱት ዶ/ር ቴድሮስ በክትባቶቹ ስርጭት ረገድ የታየውን ክፍተት ተችተዋል፡፡
“75% ያሉ ክትባቶች በ10 ሃገራት ብቻ ነው ጥቅም ላይ የዋሉት፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት የመጀመሪያ ዙር ክትባቱን ያገኙት ከ1% አይበልጡም… ዓለም ኦክስጅንን ጨምሮ ክትባቶችን፣ የምርመራ እና የህክምና ቁሳቁሶችን ለመጋራት አለመፍቀዱ፤ ሁለት መልክ ያለው፤ አንዱ ሲዘጋ አንዱ የሚከፍትበትን (ለሚጣሉ ገደቦች) የወረርሽኝ ሁኔታን እየፈጠረ ነው” ሲሉም ነው ዶ/ር ቴድሮስ የተናገሩት፡፡
ልዩነቱ የሞራል ልሽቀት እንደሆነና ይህ ከቀጠለ ወረረሽኙ ተራዛሚ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን ሊፈጥር እንደሚችልም አክለው ገልጸዋል፡፡
ከ200 ሃገራት የተውጣጡ 11 ሺ አትሌቶች እንደሚሳተፉ በሚጠበቅበት የቶኪዮ ኦሎምፒክ እስካሁን ከውድድሩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው 79 የኮሮና ኬዞች ሪፖርት ተደርገዋል፡፡