በኮሮና ምክንያት የቶኪዮ ኦሊምፒክን የመሰረዝ አማራጭ አሁንም እንዳለ የጃፓን ፖለቲከኛ ተናገሩ
የፖለቲከኛው አስተያየት ውድድሩ ላይካሔድ ይችላል በሚል በብዙዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል
የገዢው ፓርቲ ዋና ፀሐፊ “ቫይረሱን የሚያሰራጭ ከሆነ ኦሊምፒክ ለምን ያስፈልጋል?” ብለዋል
የጃፓን የገዢው ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ቶሺሂሮ ኒካይ ፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከቀጠለ እና እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ መጪውን የቶኪዮ ኦሊምፒክ መሰረዝ “እንደ አማራጭ ይወሰዳል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂድ ሱጋ የሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኒካይ ይህንን የተናገሩት በአንድ የጃፓን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ነው፡፡
ኒኪይ "ውድድሩን ማድረግ የማይቻል መስሎ ከታየ ቆም ብለን መወሰን አለብን" ያሉ ሲሆን ፣ የኮቪድ -19 ቀውስ ከፍተኛ ስጋት ሆኖ ከቀጠለ ትልቁን የክረምት ስፖርታዊ ትዕይንት መሰረዝ አማራጭ “መሆኑን” ገልጸዋል፡፡
አክለውም “ኦሊምፒኩ ቫይረሱን የሚያሰራጭ ከሆነ ፣ ታዲያ ኦሊምፒክ ለምን ያስፈልጋል?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ይሁንና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስረዛን በተመለከተ ማንኛውም ውሳኔ በወቅቱ የጤና ሁኔታ ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ኒካይ በአፅንዖት ገልጸዋል፡፡
የኒካይ አስተያየት ፣ የበሽታው ወረርሽኝ እንዳለ ሆኖ ኦሊምፒኩ በታቀደው መሠረት እንደሚከናወን ደጋግመው ከገለጹት የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይ.ኦ.ሲ) እና የቶኪዮ የውድድሩ አዘጋጆች አስተያየቶች ተቃራኒ ነው፡፡
ታዋቂው ፖለቲከኛ የሰጡት አስተያየት ፣ ውድድሩ ላይካሔድ ይችላል በሚል በብዙዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ይህን ተከትሎ ኒካይ በሰጡት አስተያየት ፣ እርሳቸው መግለጽ የፈለጉት “ኦሊምፒክ የቱንም ዓይነት ዋጋ ተከፍሎበት ይካሔዳል ማለት እንዳልሆነ” መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሐሙስ ዕለት የጃፓን የአስተዳደር እና የቁጥጥር ማሻሻያ ሚኒስትር የሆኑት ታሮ ኮኖ እንደተናገሩት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተመልካቾች ሳይታደሙ ሊካሄዱ ይችላሉ፡፡ “ኦሊምፒኩ ሊካሄዱ በሚችልበት መንገድ ይካሄዳል፡፡ ጨዋታዎቹ ያለ ተመልካች ሊከናወኑ ይችላሉ ”ሲሉ በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል፡፡
አራተኛ ዙር የኮቪድ -19 ወረርሽኝን በማስተናገድ ላይ የምትገኘው ጃፓን ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመቋቋም እንደ አንድ እርምጃ ዓለም አቀፍ ደጋፊዎች ለኦሊምፒክ ውድድር ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ ማገዷ ይታወቃል፡፡
ሰሜን ኮሪያም አትሌቶቿን ከኮሮና ተጋላጭነት ለመጠበቅ በሚል በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንደማትሳተፍ ገልጻለች፡፡
እስካሁን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁባት ጃፓን ፣ በቫይረሱ ሳቢያ 9,500 ዜጎቿን በሞት ተነጥቃለች፡፡