የለንደን ማራቶን ሊሰረዝ እንደሚችልም ተገለጿል
የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሊራዘም ለንደን ማራቶን ደግሞ ሊሰረዝ ይችላል ተባለ
በመጪው ወርሃ ሃምሌ መጨረሻ የሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እ.ኤ.አ እስከ 2020 መጨረሻ ሊራዘም እንደሚችል የሃገሪቱ የኦሎምፒክ ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡
ውድድሩ በተጠቀሰው ጊዜ እንዲካሄድ ሃገራቸው ከዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር መስማማቷን የገለጹት ሴኮ ሃሺሞቶ ውድድሩን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለማራዘም ስምምነቱ ይፈቅድልናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ሃሳቡ የዓለም አቀፉን የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውሳኔ የሚሻ ነው፡፡
በተያያዘ ስፖርታዊ ዜና በተሳታፊ ብዛት ስጋት ያደረባት እንግሊዝ ለንደን ማራቶንን ልትሰርዝ እንደምትችል ዴይሊ ሜይል አስነብቧል፡፡
ውድድሩ ”እንደ ሰደድ እሳት እተዛመተ ነው“ ባሉት የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊሰረዝ እንደሚችልም የጤና ጸሃፊው ማት ሃንኩክ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ይህን ለመወሰን የሃገሪቱ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኩል የሚወጣው ኮሮናን የመከላከል ዐቅድ ይፋ መሆን ይጠበቃል፡፡
ሌሎች ስፖርታዊ ክንውኖችን የማገድ ሃሳብ በመንግስት በኩል እንደለሌለ ግን ጸሃፊው ገልጸዋል፡፡