በዱባይ የሚካሄደው ኮፕ28 ሊጀመር 100 ቀናት ቀርተውታል
በጉባኤው የአለም ሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ
አረብ ኤምሬትስ 2023 የዘላቂነት አመት እንዲሆን አውጃለች
የ2023ቱ የአለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) ሊጀመር 100 ቀናት ቀርተውታል።
ጉባኤው ከፈረንጆቹ ህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 2023 በአረብ ኤምሬትስ ዱባይ ይካሄዳል።
በአየር ንብረት ለውጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረውን ግዙፍ አለማቀፍ መድረክ የምታስተናግደው ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን 2023 የዘላቂነት አመት እንዲሆን አውጀው የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ ነው።
በጉባኤው የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ። ከተለያዩ የአለም ክፍል የተውጣጡ ወጣቶች እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮችም አለምን እየፈተነ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ሃሳባቸውን የሚያጋሩባቸው መድረኮች ይኖራሉ።
ከ100 ቀናት በኋላ የሚጀመረው ጉባኤ አለም በ2050 ከካርበን ልቀት ነጻ ትሆን ዘንድ ሀገራት ቃል ገብተው የተፈራረሙት ሰነድ እና አፈጻጸሙ በስፋት ይመከርበታል።
የአለም ሙቀትን በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ በ2015 በፓሪስ የተደረሰው ስምምነት አፈጻጸምን በመገምገም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ጉዳዮችም ውይይት ይደረግበታል።
በዶክተር ሱልጣን አል ጃበር የሚመራው የኮፕ28 አዘጋጅ ኮሚቴም ጉባኤው የተቃና እንዲሆን ስራውን ከጀመረ የሰነባበተ ሲሆን ቀጣዮቹ አራት ነጥቦች ሊተኮርባቸው እንደሚገባ ነው ያሳሰበው።
1. የታዳሽ ሃይል ሽግግር
የበካይ ጋዝ ልቀትን የሚያስቀሩና ታዳሽ የሃይል ምንጮችን ማስፋት ላይ ማተኮር የሚለው ቀዳሚው ነው። አለም የታዳሽ ሃይል ምርቷን በሶስት እጥፍ አሳድጋ 11 ሺህ ጊጋዋት ማድረስ ይኖርባታል። በተያዘው ፍጥነት መሄድ ግን ሀገራት በ2050 ለማሳካት ካቀዱት ውጥን አያደርሳቸውም ብሏል ኮሚቴው። እናም የታዳሽ ሃይል ሽግግሩ ፈተና እና ተስፋ በኮፕ28 በስፋት ይመከርበታል።
2. የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ
አሁን ያለው የአለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ስሪት ያለፈው ክፍለዘመን እሳቤን እንጂ ወቅታዊውን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የቃኘ አይመስልም። በዚህም ምድርን ከተጋረጠባት የአየር ንብረት ቀውስ በፍጥነት መታደግ አልቻለም። አለማቀፉ የፋይናንስ ስርአት በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን መዘንጋቱን እንዳይቀጥል የሚያሳስበው የኮፕ28 አዘጋጅ ኮሚቴ ለሀገራቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ስራ በየአመቱ 1 ትሪሊየን ዶላር ሊመደብ ይገባል ብሏል። ከዚህ ውስጥ 700 ቢሊየን ዶላሩ ለታዳሽ ሃይል ልማት ሊመደብ እንደሚገባም በመጥቀስ።
3. ጤና እና የጉዳት ካሳ ክፍያ
የኮፕ28 ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የአለም ሀገራትን የጤና ሚኒስትሮች ያገናኛል። በዚህም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሰው ልጆች ላይ እያደረሱት የሚገኙት የጤና ጉዳት ይዳሰሳል። ከዚህም ባሻገር የምግብ ዋስትና ችግሮች ይዘዋቸው የመጡ ፈተናዎች ምክክር ይደረግባቸዋል። የበለጸጉት ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኗቸው አነስተኛ ነገር ግን በከፍተኛ ደረጃ ለሚጎዱ ሀገራት ካሳ ለመክፈል በግብጽ ሻርም አል ሼክ የደረሱት ስምምነትም ገቢራዊ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ውይይት ይደረጋል።
4. አካታችነት
ዱባይ ከ100 ቀናት በኋላ በምታስተናግደው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) የማይሳተፍ የህብረተሰብ ክፍል የለም። የመንግስት ባለስልጣናት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ኢንጂነሮች፣ ሃኪሞች፣ ወጣቶች፣ በተለያዩ ሀገራት ጥቅጥቅ ጫካን ከመጨፍጨፍ የሚታደጉ ህዝቦች ተወካዮች ሁሉም የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ በራሳቸው አተያይ ያጋራሉ፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ይጠቁማሉ።