በዱባይ በሚካሄደው ኮፕ28 ጉባኤ ኢትዮጵያ ምን ይዛ ትቅረብ?
አል አይን ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች የነበራትን ተሳትፎና ቀጣይ ትኩረቷ ምን ሊሆን እንደሚገባ ምሁራንን ጠይቋል
በኮፕ28 በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ዙሪያ የሚያጠነጥነው አስገዳጅ ስምምነት የማስፈጸሚያ ህጎች እንደሚጸድቁ ይጠበቃል
28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) በቀጣዩ አመት ህዳር ወር በአረብ ኢምሬትስ ዱባይ ይካሄዳል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ እየጨመረ በመጣው የዓለማችን አየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ዙሪያ የተመድ አባል ሀገራት፣ ምሁራን እና ኩባንያዎች ይሳተፋሉ፡፡
ዓለም አቀፉ የተመድ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ መካሄድ ከጀመረ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶች መጨመር ለጉባኤው መጀመር ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡
ኢትዮጵያም በዚህ ጉባኤ ላይ መሳተፍ ከጀመረች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባት ጉዳትም በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡
ለመሆኑ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ እንደ አህጉር በዚህ መድረኮች ላይ መሳተፋቸው ምን አስገኘ? በቀጣይ በሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ ስትሳተፍስ ምን ታገኛለች? እና ምን ይዛስ በጉባኤው ላይ ትሳተፋለች? ስንል የአካባቢ ጥበቃ እና አየር ንብረት ለውጥ ምሁራንን አነጋግረናል፡፡
ዶክተር በየነ ተክሉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ መከሰት ያላት አስተዋጽኦ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም በሌሎች አበርክቶ ግን በየጊዜው ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚባለው ድርቅ፣ የጎርፍ እና ውሃ መጥለቅለቅ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና ከፍተኛ ቅዝቀዜ መከሰት እና ሌሎችም ሲሆኑ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ እየተጎዳች መሆኗንም ዶክተር በየነ አክለዋል፡፡
በድርቁ ምክንያትም አርሶ አደሮች ለድህነት እየተጋላጡ፣ የእንስሳት እና የእጸዋት ዝርያዎች እየጠፉ፣ ለመሰረተ ልማት ይውል የነበረ ሀብት ለድርቅ ተጎጂዎች እንዲውል እየተገደድን ነው ይላሉ ተመራማሪው።
በየዓመቱ የሚካሄደው የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በችግሮች ዙሪያ በመወያየት ስለ መፍትሄዎች ለመምከር እድል ይፈጥራል የሚሉት ዶክተር በየነ፥ የበለጸጉ ሀገራት ግን ሀገራት በየዓመቱ ወደ ውሳኔ እንዳይመጡ እና አስገዳጅ ስምምነቶች እንዳይኖሩ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር በየነ ገለጻ የበለጸጉ ሀገራት ከባቢ አየርን የሚበክሉ የሀይል አቅርቦቶችን በመጠቀም ሀብት እያፈሩበት ያለው መንገድ እንዲቋረጥ የማይፈልጉ ሲሆን እስካሁን ላደረሷቸው ጉዳቶችም ካሳ የመክፈል ፍላጎት የላቸውም፡፡
ኢትዮጵያም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጀምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ እና ታዳሽ ሀይል መሰረተ ልማቶች ትኩረት ማድረጓን የሚናገሩት ተመራማሪው፥ ይህ ተግባር መቀጠሉን አክለዋል፡፡
የፊታችን ህዳር 2016 ዓ.ም በአረብ ኢምሬትስ ዱባይ ከተማ በሚካሄደው 28ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በተናጥል እና አፍሪካ እንደ አህጉር የበለጸጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት መቀነስ ትኩረት እንዲሰጡ ግፊት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡
በዱባዩ ጉባኤ ላይ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ዙሪያ የሚያጠነጥነው አስገዳጅ ስምምነት የማስፈጸሚያ ህጎች ይጸድቃል ብዬ እጠብቃለሁ የሚሉት ዶክተር በየነ የበለጸጉ ሀገራት በሚለቁት በካይ ጋዝ አፍሪካ ለድርቅ፣ አውሎ ንፋስ፣ የስነ ምህዳር መውደም እና ሌሎች ጉዳቶች ካሳ የምታገኝበት መንገድ እንዲቀረጽ ግፊት ሊደረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
በኮፕ28 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የበለጸጉ ሀገራትም እያደረሱት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እውቅና የሚሰጡበት እና ከበካይ ሀይል የሚያገኙትን ሀይል መቀነስ ላይ ለማተኮር ቃል የሚገቡበት መድረክ ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁም ዶክተር በየነ ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ላይ የተሳተፉት አቶ ዮናስ ገብሩ የኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ጥምረት አስተባባሪም ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት የዓየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፋዊ ሲሆን የጋራ ጥረት እና መፍትሔም የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ባንድ ጊዜ የሚከሰት እና አንድ አይነት መፍትሄ የሚፈልግ አይደለም የሚሉት አቶ ዮናስ፥ ጉዳቱን መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን በሂደት መስራት ዋነኛው መፍትሄ እንደሆነ አክለዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማትን መፍጠር፣ ችግሮችን መቀነስ የሚያስችሉ እና መላመድን የሚያበረታቱ አሰራሮችንም መከተል ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ ዮናስ፡፡
በየዓመቱ የሚካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤም ጥቂቶቹ ጥሩ ለውጥ የተገኘባቸው ናቸው የሚሉት አስተባባሪው፥ በተለይም በፓሪስ እና በግብጽ የተካሄዱት የዓየር ንብረት ጉባኤዎች በአንጻራዊነት ጥሩ ውሳኔዎች የተወሰኑባቸው ነበሩ ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ ጉባኤዎች ላይ አዝጋሚ ቢሆንም የተወሰኑ ለውጦች የታዩ ቢመስልም በተለይም በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ምክንያት የበለጸጉ ሀገራት በካይ ጋዝ የመጠቀም ፍላጎታቸው እንዲጨምር ማድረጉን አቶ ዮናስ ጠቅሰዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በግብጽ ሻርም አልሼክ ከተማ የተካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን ማካካስ የሚያስችል የጋራ ሀብት ማሰባሰቢያ ቋት እንዲመሰረት ከስምምነት ላይ መደረሱ ጥሩ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
የፊታችን ህዳር በዱባይ በሚካሄደው ኮፐ28 ጉባኤ ላይ የዚህ ስምምነት አፈጻጸም መመሪያ እንደሚጸድቅ እጠብቃለሁ ያሉት አቶ ዮናስ፥ የበለጸጉ ሀገራት ግን ስምምነቱ እንዳይተገበር የተለያዩ ሙከራዎችን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡