ነገ በሚጀመረው የኮፕ28 ጉባኤ ተጠባቂ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በዱባኤ በሚካሄደው ጉባኤ ከ97 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉ የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር ተናግረዋል
በጉባኤው በርካታ የነዳጅ ኩባንያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚፈራረሙት ስምምነት ይጠበቃል
የአረብ ኤምሬትስ ደማቋ ከተማ ዱባይ ስትዘጋጅበት የከረመችውን ግዙፍ አለማቀፍ ሁነት በነገው እለት በይፋ ታስጀምራለች።
የአለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) ፕሬዝዳንት እና የኤምሬትስ የኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር በጉባኤው ዋዜማ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዱባዩ ጉባኤ በተሳታፊ ብዛትም ሆነ በዝግጅት ታሪካዊ ሆኖ ይመዘገባል ያሉት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት፥ ጉባኤው አለምን እየፈተነ ለሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሄዎች ያስቀምጣል ብለዋል።
በጉባኤው ላይ ከ97 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ፤ ከ400 ሺህ በላይ ጎብኝዎችም ኤምሬትስን ጨምሮ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ አበረታች ስራ የሰሩ ሃገራት ተሞክሮን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኤምሬትስ በዚህ ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉ ሰዎች አየርን የማይበክሉ የትራንስፖርት እና ሌሎች መሰረተልማቶችን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች ታቀርባለች።
ታሪካዊ የነዳጅ ኩባንያዎች ስምምነት
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው በዱባዩ ጉባኤ በርካታ የነዳጅ ኩባንያዎች በ2050 የበካይ ጋዝ ልቀታቸውን ወደ ዜሮ ለማውረድ ስምምነት ይፈራረማሉ።
ስምምነቱ ያካተታቸው ነጥቦች እና የፈራሚዎቹ ቁጥር የዱባዩን ጉባኤ ታሪካዊ እንደሚያደርገውም በመጥቀስ።
“የአለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በትብብር የምንሰራበት ጊዜ ነው” ያሉት አል ጃበር፥ የአለም ሙቀት ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ በላይ እንዳይጨምር ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኤምሬትስ የኮፕ28 ጉባኤን በዱባይ ኤክስፖ ሲቲ በደማቁ ለማክበር ዝግጅቷን አጠናቃለች።
የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ የኩባንያዎች፣ የወጣት እና ሌሎች ማህበራት ተወካዮች ዱባይ በመግባት ላይ ናቸው።
ሌሎች ተጠባቂ ክስተቶች
“የጤና ቀን” የተሰኘና የዓለም ሀገራት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ሁነት ለ12 ቀናት በሚዘልቀው ጉባኤ ይካሄዳል።
ሚኒስትሮቹ የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ላይ ስለሚያደርሳቸው ጉዳቶች ዙሪያ ተወያይተው የውሳኔ ሀሳብ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
“ዓለም አቀፍ የንግድ ቀን” ደግሞ የዓለም በካይ ጋዝ ልቀት፣ የታዳሽ ሀይል ሽግግር እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር የሚደረግበት ሌላኛው ሁነት ነው።
የሀይማኖት መሪዎች የሚሳተፉበት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጋራ ሀላፊነት በሚወሰድበት ሁኔታ የሚደረገው ውይይትም የኮፕ28 አካል ነው።
ሌላኛው የጉባኤው አበይት ሁነት በዓለም የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው ህዝቦች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚመክሩበት ሲሆን፥ በተመድ የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ህዝብ ፊት ቀርበው ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡