የኮፕ 28 ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃበር ማን ናቸው?
ከ40 በላይ ሀገራትን የታዳሽ ሀይል ልማት ያማከሩት ሱልጣን ቢን አህመድ በዘርፉ የካበተ ልምድ አላቸው
የ2023 የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በህዳር ወር በአረብ ኤምሬትስ አስተናጋጅነት ይካሄዳል
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃቤርን (ዶክተር) የ2023 የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንት አድርጋ መሾሟን አስታውቃለች።
የኤምሬትስ የአየር ንብረት ጉዳዬች ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉት ሱልጣን ቢን አህመድ፥ በህዳር 30 2023 የሚጀመረውን የ2023 አለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ በፕሬዚዳንትነት ይመራሉ።
ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃቤር ማን ናቸው?
የየዠተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የንግድ እና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ሱልጣን ቢን አህመድ፥ በከየር ነብረት ለውጥ ዙሪያ በሚከናወኑ ስራዎች ስማቸው ከፊት ይነሳል።
ሁለት ጊዜ ሀገራቸውን በአለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ ወክለው የቀረቡት ሰው ከ10 በላይ መሰል አለማቀፍ ጉባኤዎች ላይ ያቀረቧቸው ሀሳቦችም የብስለታቸውን ደረጃ ስለማሳየቱ ይነገራል።
በፈረንጆቹ 2015 በፓሪስ በተደረገው ታሪካዊ ጉባኤ የተሳተፉት ሱልጣን ቢን አህመድ፥በኢኮኖሚክስና ማኔጀመንት ያካበቱት የላቀ እውቀት አላቸው።
በታዳሽ ሀይል ልማት ረገድም ሀገራቸውን ኤምሬትስ በልዩ ትኩረት እንድትሰራ በማድረግ ተሞክሮ የሚሆን ተግባርን ፈፅመዋል።
አቡ ዳቢ በፈረኝጆቹ 2006 "ማስዳር" የተሰኘ ታዳሽ ሀይል ልማት ያተኮረ ተቋም ስታቋቁም ሙሉ ሀላፊነቱን የሰጠችው ለሱልጣን ቢን አህመድ ነው።
"ማስዳር" የዩ ኤ ኢን የታዳሽ ሃይል ምንጭ ከማስፋትና ንፁህ የሃይል ምንጮችን ወደ ስራ ለማስገባት ጉልህ ሚና ሲጫወትም የእኝህ ባለሙያ ድርሻ በልዩነት ይነሳል።
ኤምሬትስ ከታዳሽ ሀይል በ2030 100 ጊጋዋት ለማመንጨት ለያዘችው ግብ መሳካት እየተጉ የሚገኙት ሱልጣን ቢን አህመድ፥
ከ40 በላይ ሀገራት (አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው) የታዳሽ ሀይል ልማት ፕሮጀክቶችን በማማከርና በመሳተፍም ትልቅ አበርክቶ አላቸው።
የአለም አቀፉ የታዳሽ ሀይል ልማት ኤጀንሲም መቀመጫውን በማስዳር ከተማ አድርጎ እንዲሰራም አድርገዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቀጣይ አምስት አመታት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ለመቆጣጠር 15 ቢሊየን ዶላር መድባ እየሰራች ነው።
ሀገሪቱ ከነዳጅ እና ብክለት የተላቀቀ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት የቢን አህመድ የረጅም ጊዜ ልምድ አስተዋፅኦው ከፍ ያለ ነው።
በ2010 ከህንዱ ተሪ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ያገኙት ሱልጣን ቢን አህመድ፥ በ2012ም የመንግስታቱ ድርጅትን "ቻም ፒዬን ኦፍ ኧርዝ" ሽልማት ወስደዋል።
በ2022 የአረቡ አለም 10. ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የገቡ ሲሆን፥ የአቡ ዳቢ ብሄራዊ የነዳጅ ኩባንያን በመምራትም ልዩ ልዩ ሽልማቶች እንደተበረከቱላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።