ጆን ኬሪ ዩኤኢ በምታዘጋጀው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለመሳተፍ ወደ አቡዳቢ ሊያቀኑ ነው
ፕሬዝዳንት ባይደን አንጋፋውን ዲፕሎማት የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መሾማቸው የሚታወስ ነው
ኬሪ በአቡ ዳቢ በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ የቀጣናው ከፍተኛ አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል
የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ዋና ከተማ አቡ ዳቢ ሊያቀኑ ነው፡፡
ጆን ኬሪ ወደ አቡ ዳቢ የሚያቀኑት ዩኤኢ በመጪው እሁድ በምታዘጋጀው ቀጣናዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጆ ባይደን ልዩ የአየር ንብረት ለውጥ መልዕክተኛ ሆነው በፕሬዝዳንቱ መሾማቸው ይታወሳል፡፡
ወደ አቡ ዳቢ የሚያደርጉት ጉዞ ከሹመቱ በኋላ የመጀመሪያቸውም ነው የሚሆነው፡፡
አንጋፋው ዲፕሎማት በባራክ ኦባማ የፕሬዝዳንትነት ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አሜሪካን ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡
አሁንም በአቡ ዳቢ በሚኖራቸው ቆይታ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ምላሾችን በተመለከተ ከባህረ ሰላጤው (ገልፍ) እና ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን ከፓሪሱ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ወጥታ የነበረችው አሜሪካ በጆ ባይደን ትዕዛዝ ወደ ስምምነት መመለሷ የሚታወስ ነው፡፡
በዩኤኢ የሚዘጋጀው ይህ ቀጣናዊ ጉባዔም አሜሪካ ከቀጣናው ሃገራት ጋር ይበልጥ ተቀራርባ ልትሰራ የምትችልበትን መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ነው ‘ዋም’ የተሰኘው የዩኤኢ የዜና አገልግሎት የዘገበው፡፡
በጉባዔው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (COP26) ፕሬዝዳንት አሎክ ሻርማ እና ሌሎችም ከፍተኛ የዘርፉ አመራሮችና ተመራማሪዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የCOP26 ዓመታዊ በመጪው ህዳር ወር በስኮትላንድ ግላስጎው ይካሄዳል፡፡