ዩኤኢ የ2023ቱ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ አስተናጋጅ ሆና ተመረጠች
የዘንድሮው የአየር ንብረት ጉባኤ በስኮትላንድ ግላስኮው በመካሄድ ላይ ይገኛል
ዩኤኢ ከብዙ አገራት ጋር ተወዳድራ ነው ለ28ኛ ጊዜ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ ያሸነፈችው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) በፈረንጆቹ 2023 የሚካሄደውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ28) ለማስተናገድ ተመረጠች፡፡
ዩኤኢ ከ2 ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ቀደም ብላ አስታውቃ ፍላጎቱ ካላቸው ሌሎች ሃገራት ጋር ስትወዳደር ነበር፡፡
የዩኤኢ ምክትል ፕሬዘዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱምእንዳስታወቁት አገራቸው በተመድ የአየር ንብረት ስምምነት ጉባኤ ስር የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመርጣለች፡፡
አገሪቱ ይህንን ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገቸው ላለው ጥረት እውቅና የሚሰጥ ነውም ተብሏል፡፡
የአቡዳቢ አልጋወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በበኩላቸው አገራቸው የእድሎች፣ የትብብር እና የመነሳሳት ተምሳሌት መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ምድራችንን ከከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ለመጠበቅ የሚመክረውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዩኤኢ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗንም አልጋወራሹ አክለዋል፡፡
ዩኤኢ ለአረንጓዴ ልማት እና ለዘላቂ የአየር ንብረት ለውጥ የሰጠችውንና የሰራቻቸውን ስራዎች ከግምት ውስጥ በማስገባትም ነው የተመረጠችው፡፡
ዩኤኢ በስኮትላንድ ግላስኮው በመካሄድ ላይ ባለው ኮፕ26 የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ ወሳኝ የመሪነት ሚናን ስትጫወት ነበረ፡፡
ኮፕ26 ባለፈው ዓመት ነበር የሚካሄደው፤ ሆኖም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ወደዘንድሮ ተላልፎ በግላስኮው በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡